በጎንጂ ቆለላ ወረዳ በፀጥታ ኃይሉ እና በኅብረተሰቡ ተሳትፎ አንጻራዊ ሰላም መገኘቱ ተገለጸ።

21

ባሕር ዳር: ግንቦት 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ጎጃም ዞን የጎንጂ ቆለላ ወረዳ የመንግሥት ሠራተኞችን የሥራ አፈጻጸምን በመለካት በሰላም እና ፀጥታ ዙሪያ ያላቸውን ቁርጠኝነት ገምግሟል።

የጎንጂ ቆለላ ወረዳ አሥተዳደሪ ጌታቸው ጋሻው በወረዳው መሽገው ሕዝቡን ሲዘርፉ እና ሲያንገላቱ የቆዩት የፅንፈኛው ኃይል አባላት በፀጥታ ኃይላችን እና በኅብረተሰባችን በተወሰደው ተከታታይነት ያለው ሕግ የማስከበር ሥራ አንጻራዊ ሰላም ሰፍኗል ብለዋል። አሥተዳዳሪው አክለውም የመንግሥት ሠራተኛው በሰላም እና ፀጥታ ዙሪያ ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል። ለወራት ዝርፊያ እና ግድያዎችን በመፈፀም ሕዝባችንን መውጫ እና መግቢያ ያሳጡት ፅንፈኞች ላይ እየተወሰደ ያለውን እርምጃ የጋራ ማድረግ ይገባልም ብለዋል።

የጎንጂ ቆለላ ወረዳ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ሻሽቱ አሰፋ“ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት ነው፤ ያለ ሰላም መኖርም ኾነ መሥራት የማይቻል መኾኑን በመገንዘብ የመንግሥት ሠራተኛው ለሰላም ቅድሚያ መስጠት አለበት ብለዋል። በፅንፈኞች እንደ ሕዝብ የተነጠቅነውን ሰላማችንን ለመመለስ እና ሕዝባችንን ከችግር ለማውጣት በፀጥታ ሥራ ላይ መሳተፍን ትኩረት ልንሰጠው ይገባል” ሲሉ ተናግረዋል።

ወይዘሮ ሻሽቱ በሰላም መደፍረስ ምክንያት እንደ ክልል የተቀዛቀዘው ኢኮኖሚ ለማነቃቃት ከፀጥታ ሥራው ጎን ለጎን የልማት ሥራ በመሥራት የሁሉም መሠረት የኾነው ሰላማችንን በአፋጣኝ ለማረጋገጥ የመንግሥት ሠራተኛው ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት እና ከዚህ ያለፈ ኃላፊነት በመወጣት መጓደሎች ሲኖሩም ተጠያቂነት እንደሚኖር አረጋግጠዋል።

በቀጠናው የተሰማራው የምስራቅ ዕዝ ክፍለ ጦር አዛዥ ኮሎኔል ዓለም ታደለ “የፅንፈኛው ቡድን በወረዳው የበርካታ ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል፤ ንብረት በመዝረፍ እና በማውደም ሕዝቡን የድህነት አረንቋ ውስጥ ከትቷል ብለዋል። የሰሜን ጎጃም ዞን መንግሥት ኮሙኒኬሽን መረጃ እንደሚያመለክተው መከላከያ ሠራዊቱ እና የክልሉ የፀጥታ ኃይል ሕዝቡን ለመታደግ ውድ ሕይወቱን እየገበረ ይገኛል፤ የመንግሥት ሠራተኛው በፀጥታ ሥራው ላይ በመሳተፍ አሥተዳደሩን መደገፍ እና ሕዝቡን በቁርጠኝነት ማገልገል ይገባዋል ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኅብረተሰብ ተወካዮች በአጀንዳ ሃሳቦች ላይ እየተወያዩ ነው፡፡
Next articleየቻይናው ኩባንያ በባሕር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ምርት ማምረት ጀመረ፡፡