የክልሉን አንፃራዊ ሰላም ወደ አስተማማኝ ደረጃ በማሸጋገር ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎች ላይ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ አሳሰበ፡፡

33

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በሚቀጥሉት 100 ቀናት የሚተገበሩ ቁልፍ ዕቅዶች ተለይተው ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተገብቷል፡፡ የዕቅዱ ዋና ዓላማ በክልሉ ያጋጠመውን የሰላም እና የጸጥታ ችግር በመፍታት ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎች ላይ ርብርብ ማድረግ ነው፡፡

ክልሉ አሁን ያለበትን አንፃራዊ ሰላም ወደ አስተማማኝ ሰላም ለማሸጋገር በቀጣይ 100 ቀናት በዕቅድ በተያዙ ተግባራት ዙሪያ ከሁሉም ዞኖች፣ ከተማ አሥተዳደሮች እና የወረዳ መሪዎች ጋር የጋራ መግባባት ላይ ተደርሶ ስምሪት ተደርጓል ብሏል የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ፡፡ ቢሮው በክልሉ ያጋጠመን ችግር ለመቅረፍ የተከናወኑ ተግባራትን በመገምገም ውጤታማ እና በክፍተት የታዩትን በመለየት ሰፊ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ማከናወን የዕቅዱ ተቀዳሚ ግብ ተደርጎ ተወስዷል ብሏል፡፡

በተለይ በሰላም መደፍረስ ምክንያት የተፈጠሩ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ስብራቶችን ለመጠገን የሁሉንም ርብርብ እና ትብብር የሚጠይቅ ተግባር ነው፡፡ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች በቀጣይ 100 ቀናት በተቀናጀ እንቅስቃሴ የየአካባቢውን ሰላም ማረጋገጥ፣ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው መመለስ፣ የመኽር ሰብል ልማት ሥራን ማሳለጥ እና ወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ ትኩረት የሚሰጥባቸው ጉዳዮች እንደኾኑ ገልጿል፡፡

በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የገጠመውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት እና የልማት ሥራዎችን ለማስቀጠል የኅብረተሰቡን ተሳትፎ ለማረጋገጥ ከዚህ ቀደም በተዘጋጁ ተደጋጋሚ መድረኮች 30 ሚሊዮን የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተደራሽ ያደረገ ውይይት መካሄዱን አስታውሷል፡፡ ይሁን እንጅ የተፈጠረው ሰላም አሁንም ቢኾን አስተማማኝ ደረጃ ላይ ባለመድረሱ በቀጣይ 100 ቀናትም በሰላም ዙሪያ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከወጣቶች፣ ሴቶች እና ከልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይቱ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይኾናል ነው ያለው፡፡

በክልሉ በጸጥታ ምክንያት የተቋረጡ እና የተጓተቱ የልማት ሥራዎች በትኩረት እንዲጠናቀቁ ለማድረግ እንደ ክልል አቅጣጫ የተቀመጠ ሲኾን በመጠናቀቅ ላይ ያሉ የልማት ሥራዎችንም በማስመረቅ ኅብረተሰቡ በባለቤትነት ስሜት እንዲጠብቃቸው የማድረግ ሥራ እንደሚሠራም ገልጿል። ማኅበረሰቡ የጸጥታ ችግሮችን በመፍታት ሂደት የራሱን አስተዋፅኦ እንዲያበረክት የሚጠበቅበት ሲኾን በክልሉ የተፈጠረውን አለመረጋጋት ተከትሎ የተባባሰውን የኑሮ ውድነት እና ሥራ አጥነት ለማሻሻል መላው የመንግሥት መዋቅር እና ሕዝቡ ንቁ ተሳትፎ ሊያደርግ ይገባል ብሏል፡፡

እንደ መንግሥት አሉ የተባሉ አቅሞችን ሁሉ በመጠቀም ምርት እና ምርታማነት ላይ በስፋት በመሥራት በአነስተኛ ወጪ እና መሬት በውስን ጊዜ ማምረት ላይ ትኩረት እየተደረገ ሲኾን የበጋ መስኖ ስንዴን የማልማት እና የሌማት ትሩፋት ውጤቶችን ለኅብረተሰቡ ተደራሽ የማድረግ ሥራዎች አበረታች ውጤት የተመዘገበባቸው ስለመኾናቸው አስገንዝበዋል፡፡

የሥራ ዕድል ፈጠራውን ከሌማት ትሩፋት ጋር በማስተሳሰር በእንስሳት እና በእንስሳት ተዋጽኦ ማለትም በወተት፣ በእንቁላል እና በማር ምርቶች የገበያ ክፍተቱን ለመሙላት እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገቡ በመኾናቸው ተጠናክረው ይቀጥላሉ ነው ያለው፡፡ የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳለው በተለያዩ መድረኮች በሕዝብ የተነሱ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ተከታትሎ ለመፍታት በአጭር፣ በመካከለኛ እና በረዥም ጊዜ ምላሽ የሚያገኙበትን ዕቅድ በማስቀመጥ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የተገባ ሲኾን ኅብረተሰቡ የክልሉን ሰላም በማረጋገጥ ረገድ የሚኖረው ሚና በምንም የማይተካ በመኾኑ ለተግባራዊነቱ በጋራ መረባረብ ይገባል ብሏል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአማራጭ ወደብ ለማግኘት በሚያስችሉ ዓለም አቀፋዊ ተሞክሮዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ውይይት እየተካሄደ ነው።
Next articleየከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ያዘጋጀው 2ኛው ቢግ 5 የግንባታ አውደ ርዕይ ተጀመረ።