አማራጭ ወደብ ለማግኘት በሚያስችሉ ዓለም አቀፋዊ ተሞክሮዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ውይይት እየተካሄደ ነው።

18

አዲስ አበባ: ግንቦት 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያን አማራጭ ወደብ ለማግኘት በሚያስችሏት ዓለም አቀፋዊ ተሞክሮዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ውይይት እየተካሄደ ነው። በውይይቱ ላይ የቀይ ባሕር ደኅንነት እና ቀጣናዊ ትርምስ በማርገብ ረገድ ኢትዮጵያ ትልቅ ሚና እንዳላት የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ገልጿል።

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ በቀይ ባሕር ቀጣና ያለውን ፈጣን እና ተለዋዋጭ የደኅንነት ኹኔታ ያገናዘበ ሥራ መሥራት ይጠይቃል ብለዋል። ቀይ ባሕር ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ፣ ወታደራዊ እና ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያለው በመኾኑ ተከታይነት ያላቸውን ውይይቶች ማካሄድ አስፈላጊ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከጥንት ዘመን ጀምሮ የቀይ ባሕር የባሕር መስመር ተጠቃሚ እንደኾነች ተገልጿል፡፡ የአሁኑ ትውልድ ይህንን በመገንዘብ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ የመጠቀም መብቷ እንዲረጋገጥ ትውልዱ ሚናውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተሩ፡፡ የቀይ ባሕር አካል የኾነው “ባብሄል መንደብ” ቀይ ባሕርን እና ኤደን ባሕረ ሰላጤን እንዲሁም አፍሪካን እና እስያን የሚያገናኝ እና የስዊዝ ካናልን የሚያካትት ቀጣና ነው። በመኾኑ በዚህ ቀጣና ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ ከማንኛውም ተቋም እና ሀገራት ጋር ለመሥራት ዝግጁ መኾኗን ዳይሬተሩ ገልጸዋል።

የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችን ጨምሮ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላትን ያካተተ በቀይ ባሕር ጂኦፓለቲካ ዙሪያ ያሉ ሀገራት እና የደኅንነት ሁኔታ መሰረት ያደረገ ውይይት ተደርጓል፡፡ ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ውይይት እንደተካሄደ በመድረኩ ተገልጿል።

ዘጋቢ፡- ዳንኤል መላኩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኢትዮጵያ እያደገ በመጣው የግንባታ ዘርፍ ለያዘችው 10 ዓመት ዕቅድ ስኬት የውጭ አጋሮች ጋር አብራ መሥራት ትፈልጋለች” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
Next articleየክልሉን አንፃራዊ ሰላም ወደ አስተማማኝ ደረጃ በማሸጋገር ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎች ላይ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ አሳሰበ፡፡