
ባሕር ዳር: ግንቦት 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በታዳጊ ሀገራት ፍትሐዊ እና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት በተሟላ መልኩ ለማቅረብ የዓለም ጤና ድርጅትን ጨምሮ የሚመለከታቸው አጋሮችና ባለድርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርባለች። በስዊዘርላንድ ጀኔቫ እየተካሄደ ባለው 77ኛው የዓለም ጤና ጉባዔ ላይ ኢትዮጵያ በተለያዩ የጤና ጉዳዮች ላይ መግለጫ አቅርባለች፡፡
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ ለጉባዔው ባደረጉት ንግግር የጤና አገልግሎት የዜጎች ሰብዓዊ መብት መሆኑን ኢትዮጵያ በጽኑ ታምናለች ብለዋል፡፡ ዓለም አቀፍ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ማንንም መተው የለበትም በማለት ገልጸዋል። ምንም ዓይነት ልዩነት እና ድንበር ሳይኖር ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት መስጠት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በኢትዮጵያ ቤተሰብን ማዕከል በማድረግ በተሠሩ የጤና ሥራዎች በተለይም በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም በገጠር እና ራቅ ባሉ አካባቢዎች ላሉ ዜጎች ጭምር ግንዘቤ በመፍጠር እና መሰረታዊ የጤና አገልግሎቶችን በማቅረብ አመርቂ ውጤቶች መገኘቱን ገልጸዋል። በተለይም የእናቶች እና የሕጻናት ጤናን በማሻሻል ሞትን መቀነስ፣ ኮቪድ- 19ን ጨምሮ ተላላፊ የሆኑ በሽታዎችን ከመከላከል እና መቆጣጠር አንጻር በተሠሩ ሥራዎች ቀላል የማይባል ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል፡፡
ሆኖም ግን የጤና አደጋዎችን የሚቋቋም እና ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ ጠንካራ የጤና ሥርዓት እንዲገነባ አሁንም ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል ማለታቸውን ከሚኒስቴሩ ያተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡ የጤና አገልግሎት የዜጎች ሰብዓዊ መብት ሆኖ እያለ በቂ ሃብት ባለመኖሩ እና በሌሎች ምክንያቶች ኢትዮጵያን ጨምሮ በታዳጊ ሀገራት ለዜጎች ፍትሐዊ እና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት በተሟላ መልኩ ለማቅረብ አስቸጋሪ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም የዓለም ጤና ድርጅትን ጨምሮ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አጋር ድርጅቶች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። በተመሳሳይ በዓለም አቀፍ የጤና ሽፋን ተደራሽነት፣ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች፣ ቀጣይነት ያለው የጤና ፋይናንሲንግ እና የአባል ሀገራት አስተዋጽ እና ሌሎች አጀንዳዎች ላይ የተዘጋጁ መግለጫዎች በኢትዮጵያ ልዑክ ቡድን ተወካዮች ቀርቧል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
