ስማርት ሲቲ

101

ባሕር ዳር: ግንቦት 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ስማርት ሲቲ ማለት አገልግሎትን ለማዘመን፣ መረጃን ለመለዋወጥ፣ የአገልግሎት ጥራትን ለማሻሻል እና የዜጎችን ፍላጎት ለማርካት የሚያስችል የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን መሠረተ ልማት የተዘረጋለት እና አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ የታገዘ ከተማ ማለት ነው።
ስማርት የሆነ ከተማ አገልግሎቶችን ውጤታማ ያደርጋል፣ ለምጣኔ ሀብት እድገት ጉልህ ሚና ይጫወታል እንዲሁም የሰዎች ሕይዎት ቀላል እና ምቹ እንዲኾን ያደርጋል።

አንድን ከተማ ስማርት ለማለት ሊሟሉ የሚገባቸው ቅድዳ ዝግጅቶች አሉ። በቴክኖሎጂ የታገዘ መሠረተ ልማት፣ አካባቢያዊ ተስማሚነት፣ ዘመናዊ የከተማ ልማት እቅድ፣ የሚዘረጉ ሥርዓቶችን መተግበር የሚችል ባለሙያ እና ተገልጋይ ያስፈልጋል። የስማርት ሲቲ ውጤታማነት የሚለካው ከተሞች በተለያዩ ዘርፎች ባሏቸው የአገልግሎት አሰጣጥ ትስስር እና ለዜጎች በሚያቀርቡት ምቹ እና ቀልጣፋ አገልግሎት ነው።

ስማርት ሲቲ ሥርዓት ውስጥ መሠረታዊ የሚባሉ በበይነ መረብ የተሳሰሩ መሳሪያዎች (አይ. ኦ. ቲ )፣ መረጃ የሚተነትኑ መተግበሪያዎች እና በትስስር ሥርዓት ውስጥ አልፈው የሚመጡ መረጃዎችን የምንቆጣጠርበት ማዕከላዊ ጣቢያ በጣም ወሳኝ የሚባሉ ግብዓቶች ናቸው። ከሁሉም በላይ ግን አይ.ኦ.ቲ ለከተማ ዝማኔ እጅግ በጣም ጠቃሚ ነው። ምክንያቱም አይ.ኦ.ቲ (በበይነ መረብ በመታገዝ መረጃ የሚለዋወጡ መሳሪያዎች) ወደ ማዕከላዊ የቁጥጥር ጣቢያ መረጃን በመላክ ከርቀት ግንኙነት ማድረግ የምንችልበትን ሥርዓት ይፈጥራሉ። በማዕከላዊ ጣቢያ የሚቀመጥ መረጃ የኩነቶችን የረጅም ጊዜ ታሪክ በማጥናት ለትንበያ አገልግሎት ይጠቅማል።

በየትኛውም ዓይነት የስማርት ሥርዓት ውስጥ እንዳለው ሁሉ ስማርት ስቲ አሁናዊ፣ በየትኛውም ቦታ እና በማንኛውም ጊዜ አገልግሎት የሚያሰጥ ሥርዓት አለው። በዘመነ የከተማ ሥርዓት ውስጥ አንድን አገልግሎት በፈለግንበት ሰዓት፣ በየትኛውም ቦታ እና በማንኛውም ጊዜ ማግኘት እንችላለን። ስማርት ሲቲ የበለጠ ሲዘምን እና የአይ.ኦ.ቲ መገልገያዎች በስፋት ሲተዋወቁ የእለት ከእለት ሕይዎታችን እጅግ ምቹ እና ቀላል ይኾንልናል። በየትኛውም ቦታ ኾነን የኩሽናችንን ምድጃ፣ የቤታችንን መብራት፣ ቴሌቪዥን፣ ቬንትሌተር በርቀት ኾነን መቆጣጠር የሚያስችል ሁኔታ ይፈጠራል።

ቤታችን ላይ ባስቀመጥነው የደኅንነት ካሜራ በየትኛውም ቦታ ኾነን ጥበቃ የምናዳርግበት እድል ይሰጣል በተጨማሪም ወደ ተቋማት ሳንሄድ አገልግሎቶችን በስልክ የምናገኝበትን ሁኔታ ይፈጥራል። በተለያዩ መተግበሪያዎች ላይ ያሉ ቻት ቦቶችን (በሰው ሰራሽ መንገድ ማሽኖች ከሰዎች ጋር በጥያቄ እና መልስ ተግባቦት የሚፈጽሙበት መንገድ) በመጠቀም ተቋማዊ አገልግሎትን በጊዜ፣ ቦታ እና ሁኔታ ሳንገደብ ማግኘት እንችላለን።

በሀገራችን የተጀመሩ ዲጂታል የአገልግሎት ክፍያ መፈፀሚያ መንገዶች፣ የመንገድ ዳር የደኅንነት ካሜራዎች፣ ሞባይል ባንክ እና መሰል አገልግሎቶች ተጠቃሽ እና በቅርብ ያሉን ማሳያዎች ናቸው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ያለገደብ ድጋፍ ማድረግ የሚያስችል መተግበሪያ ይፋ ሆነ።
Next articleኢትዮጵያ በታዳጊ ሀገራት ፍትሐዊ እና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለማቅረብ ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ አቀረበች።