
ባሕር ዳር: ግንቦት 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ያለገደብ ድጋፍ ማድረግ የሚያስችል መተግበሪያ ይፋ ኾኗል።
መተግበሪያው በተለይም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በቀጥታ ድጋፍ እንዲያደርጉ የሚያስችል ነው ተብሏል።
መተግበሪያውን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኅብረተሰብ ተሳትፎ ማሥተባበሪያ ምክር ቤት እና የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ የግድቡ ግንባታ ከተጀምረበት ጊዜ አንስቶ ባንኩ ከ320 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ አድርጓል። ከዚህ ባለፈም ለግድቡ የሚሰጠው ብድር 9 በመቶ መድረሱን አመላክተዋል፡፡
አሁን ላይ (Itsmydam.com) የተሰኘውን መተግበሪያ አሻሽሎ በማዘጋጀት ኢትዮጵያውያን ገንዘብ በማዋጣት ሌሎች እንዲያዋጡ ብሎም ድጋፍ የሚያደርጉበት ሥርዓት መዘርጋቱንም ጠቁመዋል።
መተግበሪያው ኢትዮ-ዳይሬክት ከተሰኘው መተግበሪያ ጋር የተሳሰረ በመሆኑ በውጭ የሚገኙ ዜጎች መሳተፍ እንዲችሉ የሚያደርግ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የግድቡ ግንባታ 96 በመቶ መድረሱን ያነሱት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጅነር አሸብር ባልቻ ግድቡን ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅ ከ40 ቢሊዮን ብር በላይ ወይም 850 ሚሊየን ዶላር የሚያስፈልግ መሆኑን አንስተዋል።
“የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በኢትዮጵያውያን ያልተቋረጠ ተሳትፎ ለዚህ ደርሷል” ያሉት የግድቡ የኅብረተሰብ ተሳትፎ ማሥተባበሪያ ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርሄ (ዶ.ር) በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እስካሁን ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ድጋፍ አድርገዋል ብለዋል።
የዲያስፖራው ማኅበረሰብ ያልተቋረጠ ድጋፍ እያደረገ መኾኑን በማንሳት መተግበሪያውን በመጠቀም የቀረውን ግንባታ ለማጠናቀቅ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር በላይነህ አጥላው የመተግበሪያው ወደ ሥራ መግባት ዲያስፖራው በቀጥታ ድጋፍ ማድረግ የሚችልበትን ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
ኤፍቢሲ እንደዘገበው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ ግድቡ እስከ የካቲት ወር 192 ቢሊየን ብር ወጪ የወጣበት መሆኑን ገልጸዋል። የግድቡ ዋና ዋና ሥራዎች በተያዘው ዓመት እንደሚጠናቀቁም ጠቁመዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!