“ቤተ ክርስቲያን ፈተናን መሻገር የሚያስችል ተቋም መፍጠር ይኖርባታል” ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

25

አዲስ አበባ: ግንቦት 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የ2016 ቅዱስ ሲኖዶስ ርክበ ካህናት ምልዓተ ጉባኤ ዛሬ መጀምርን አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር “ቤተ ክርስቲያን በሁለተናዊ ፈተናዎች፣ በፍቅረ ሢመት እና እራስን በራስ የመሾም አባዜ ፈተና ተጠምዳለች፤ ይህን ፈተና መሻገር የሚያስችል ተቋም መፍጠር ይኖርብናል” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በቤተ ክርስቲያን ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ እልባት የሚሰጥበት ምልዓተ ጉባኤ በመካሄድ ላይ ነው።

ቤተ ክርስቲያኗ በፈተና ውስጥ እያለፈች መኾኑን ያነሱት ቅዱስነታቸው የቤተ ክርስቲያኗ ዋናው ፈተና ከቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚመጣ መኾኑን አንስተዋል። ይህ ችግር አሁንም ቀጥሏል፤ አስተማማኝ ሰላም ለማምጣት የሚያግዝ ተቋም መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል።

ይህ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ሀገር እና ቤተክርስቲያንን የሚያሻግር መፍትሔ ማምጣት አለበት ሲሉም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ አስገንዝበዋል።

ይህን ችግር ማነው የሚፈታው እኛ ኢትዮጵያውያን ለችግሮቻችን መፍትሔ ማምጣት ለምን ተሳነን የሚለው ሊሰመርበት ይገባል ነው ያሉት።

ፈተናውም ከተወሰነ አቅጣጫ ብቻ የሚመጣ ሳይኾን ከብዙ አቅጣጫ እንደኾነ አስረድተዋል፡፡ ይህ ፈተና ከቤተ ክርስቲያን አልፎ እንደ ሀገር የሚያስከትለው አደጋ ከፍተኛ በመኾኑ ለሰላም አበክሮ መሥራት ይገባል ነው ያሉት ቅዱስነታቸው።

ይህ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ለቤተ ክርስቲያን እና ለሀገሪቱ የሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ማስተላለፍ ይኖርበታል ሲሉም አሳስበዋል።

ዘጋቢ፡- አየለ መስፍን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ካንፓኒዎች ጋር ተወያዩ።
Next articleለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ያለገደብ ድጋፍ ማድረግ የሚያስችል መተግበሪያ ይፋ ሆነ።