
ባሕር ዳር: ግንቦት 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የተቋማት ቀጣይ የበጀት ጥያቄ የሀገሪቱን አቅም ያገናዘበ እና የገንዘብ ሚኒስቴር ያስቀመጠውን የገንዘብ ጣሪያ ያማከለ መኾን እንደለበት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳስቧል። ቋሚ ኮሚቴው ከፌዴራል ዋና ኦዲተር፣ ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ከዳኞች አሥተደደር ጉባኤ፣ ከሸሪዓ ፍርድ ቤት እና ከፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሥራ ኀላፊዎች ጋር በ2017 በጀት ዓመት የኘሮግራም በጀት ዕቅድ ላይ ተወያይቷል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ደሳለኝ ወዳጄ በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት ተቋማቱ በቀጣይነት የሚያከናውኗቸውን የተለያዩ መደበኛ ሥራዎች በተሻለ መንገድ ለማሳለጥ የሚያስችል በጥናት የተደገፈ የበጀት እቅድ በማዘጋጀት የተቋቋሙበትን ዓላማ ማሳካት እንደሚገባቸው አሳስበዋል። የሀገሪቱን የመክፈል አቅም ባገናዘበ እና የገንዘብ ሚኒስቴር በሚያዘጋጀው የበጀት ጣሪያ መሰረት እንዲሁም የዋጋ ግሽበቱን ከግምት ያስገባ ወጪ ቆጣቢ የበጀት አሠራር መንደፍ እንደሚገባም ሰብሳቢው ተናግረዋል።
የቋሚ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው ተቋማቱ ለቀጣይ ዓመት የሚይዙት የመደበኛ እና የካፒታል በጀት በዋነኛነት ሀገሪቱ በራሷ አቅም የምታሟላው እና የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መኾን አለበት ብለዋል። የፍትሕ ተቋማትን ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ከማድረግ ጎን ለጎን ተቋማቱ ወቅቱን በዋጁ የቴክኖሎጂ ግብዓቶች በማስተሳሰር ለአገልጋዮች እና ለተገልጋዮች ምቹ የኾነ የሥራ አካባቢ ለመፍጠር እየተሠራ እንደኾነ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አበባ እንቢአለ ገልጸዋል።
የፍትሕ ሥርዓቱን ከማዘመን አኳያ ዘመናዊ የኾኑ የስማርት ፍርድ ቤት እና ከኢንሳ እና ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር የተለያዩ አፕልኬሽኖችን በማበልጸግ እና ሰፊ አካባቢ በሚሸፍኑ አውታረ መረብ ለማስተሳሰር እየተሠራ እንደኾነም ምክትል ፕሬዚዳንቷ ተናግረዋል። በውይይቱ የተቋማቱ የ2016 ዓ.ም የዘጠኝ ወር የበጀት አፈጻጸም ተገምግሟል። ከሰው ሃብት አደረጃጀት እና ሥልጠና፣ ከሕንጻ ግንባታ እና ኪራይ እንዲሁም የተቋማቱ የቀጣይ ዓመት የበጀት ጥያቄን በመመርመር በሚስተካከሉ እና በሚጨመሩ ጉዳዮች ላይ ምክክር ማድረጉን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!