“የተዛቡ ትርክቶችን ፈጥኖ ማረም፤ አዳዲስ የተዛቡ ትርክቶች እንዳይፈጠሩም መጠንቀቅ ያስፈልጋል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

76

ባሕር ዳር: ግንቦት 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በክልሉ ወቅታዊ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ርእሰ መሥተዳድሩ በማብራሪያቸው የተዛባ ትርክትን በተመለከተ በሰጡት ሀሳብ የአማራ ሕዝብ የተዛባ ትርክት እንዲስተካከልለት የቆየ ጥያቄ እንዳለው ይታወሳል። ይሄን ለመፍታት መንግሥት አጀንዳ አድርጎ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ በነበረው የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት የኢትዮጵያን ሕዝብ የሚያስተሳስሩ፣ በታሪኩ የሚኮራባቸው፣ ለወደፊቱም ትውልድ ጥሩ መነሻ ኾነው የሚያገለግሉ ጉዳዮች መኖራቸውን ተናግረዋል። በተቃራኒው ደግሞ የሕዝብ አንድነትን፣ አብሮነትን፣ የሀገር አንድነትን የሚጎዱ ጉዳዮች መኖራቸውን ገልጸዋል። ለአሁን ብቻ ሳይኾን ወደፊት በጋራ መገንባት ለምንፈልጋት ኢትዮጵያ የማይበጁ የተዛቡ ትርክቶች አሉ ብለዋል።

ለኢትዮጵያ ሕዝብ አብሮነትን የሚጎዱ አባባሎች፣ የፖለቲካ ትንታኔዎች፣ የታሪክ አጻጻፎች መኖራቸውን አንስተዋል። “የተዛባ ትርክት ተጎጂ ያደረገን እንደ ሀገር ነው” ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን አንድነቱ የተጠናከረ የለማ ማኅበረሰብ እንፈልጋለን፣ የበለጸገች፣ ክብሯ የተጠበቀች ሀገር እንፈልጋለን ነው ያሉት። የጋራ ራዕይ እና ውስጣዊ አንድነት ያለው ሕዝብ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

የተዛቡ ትርክቶች የሕዝብን አንድነት በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያላሉም ገልጸዋል። የተዛባ ትርክት የአማራ ክልል ችግር ብቻ አለመኾኑም አመላክተዋል። ሁሉንም ማስተካከል ስንችል ጠንካራ ትስስር ያለው፣ የጋራ ራዕይ ያለው፣ ለጋራ ራዕዩ የሚሠራ ማኅበረሰብ መፍጠር እንችላለን ብለዋል። በጋራ የሚገለጽ የጋራ ማንነት አለን ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ማንነታችንን ከምንነታችን ጋር አዋሕደን መሄድ አለብን ነው ያሉት። የተዛባ ትርክትን ማረም እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። “የተዛቡ ትርክቶችን ፈጥኖ ማረም፤ አዳዲስ የተዛቡ ተርክቶች እንዳይፈጠሩም መጠንቀቅ ያስፈልጋል” ብለዋል ርእሰ መሥተዳድሩ። ከዚህ ቀደም የነበረውን የተዛበ ትርክት ለማረም ብለን ለቀጣይ ትውልድ የሚተርፍ ሌላ የተዛባ ትርክት ከመፍጠር መጠንቀቅ አለብን ነው ያሉት።

በክልሉ ከሌሎች ክልሎች እና በክልሉ ውስጥ በልዩ ልዩ ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመመለስ ውይይቶች ተደርገው አቅጣጫ መቀመጡንም ተናግረዋል። በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ከሌሎች ክልሎች የተፈናቀሉ ወገኖችን የመመለስ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። ተፈናቃዮችን የመመለሱ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት። የተመለሱትን የአካባቢው ማኅበረሰብ በፍቅር እንደተቀባላቸውም ተናግረዋል። በክልሉ ውስጥ የተፈናቀሉ ወገኖችን ለማቋቋም ጥረት እየተደረገ መኾኑንም ተናግረዋል።

በክልሉ ሕዝብ የሚነሱ የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ በስፋት መሠራቱንም ተናግረዋል። ከፍላጎቱ አንጻር በቂ ባይኾንም በርካታ የልማት ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል። በጸጥታ ችግሩ ምክንያት የተስተጓጎሉ የልማት ሥራዎች መኖራቸውን አንስተዋል። በግጭቱ ምክንያት 148 የሚኾኑ ትራንስፎርመሮች ተጎድተዋል፣ መብራት በሚያስተላልፉ ምሰሶዎች ላይም ጉዳት ደርሷል ነው ያሉት።

የመብራት መሠረተ ልማቶች በፍጥነት እንዲመለሱ መሠራቱን ተናግረዋል። ርእሰ መሥተዳድሩ ከኢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገና የተሠሩት የመብራት መሠረተ ልማቶች ግጭት ባይኖር ላልደረሳቸው አካባቢዎች ይደርሱ እንደነበር ነው ያመላከቱት።

ፎቶ- ከፋይል

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ እሴት የተጨመረባቸውን ምርቶች ሀገራችን ለውጭ ገበያ እያቀረበች ነው” የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል
Next articleተቋማት የሚይዙት በጀት ሀገሪቱ በራሷ አቅም የምታሟላው እና የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መኾን እንዳለበት የቋሚ ኮሚቴው አባላት አሳሰቡ፡፡