
አዲስ አበባ: ግንቦት 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት የመንግሥት እና የግሉ ዘርፍ ሚና ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ አካሂዷል። በመድረኩ በአምራች ኢንዱስትሪዎች ዙሪያ የሚስተዋሉትን ችግሮች መሠረት በማድረግ የመፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ ለመወያየት የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ የአምራች ኢንዱስትሪ ባለቤቶች፣ የአምራች ኢንዱስትሪ ማኅበራት መሪዎች ተገኝተዋል።
በውይይቱም በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ያጋጠሙ ችግሮች እና ስኬቶች እንዲሁም የአምራች ኢንዱስትሪዎች ማነቆዎች ተዳስሰዋል። በውይይቱ ላይ የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በተሠሩ ሥራዎች እና ባጋጠሙ ችግሮች ላይ ውይይቶችን ማካሄድ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ሚኒስትሩ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ተማምኖ መሥራት፣ ቅንጅትን ማጠናከር እና ተደጋግፎ መሥራት ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ ይረዳል ብለዋል።
የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ በሚጠበቀው ልክ ገቢ እያስገኘ እንዳልኾነ የገለጹት ሚኒስትሩ ቅንጅታዊ አሠራሮችን በማጠናከር ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ ይገባል ነው ያሉት። በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ እሴት የተጨመረባቸውን ምርቶች ለውጭ ገበያ እያቀረበች መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ችግሮችን በጋራ በመፍታት ኢትዮጵያን በጠንካራ ኢኮኖሚ ላይ መገንባት እንደሚያስፈልግም ነው የተናገሩት።
ዘጋቢ፡- ራሔል ደምሰው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!