
ባሕር ዳር: ግንቦት 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ በአዲስ አበባ አስጀምሯል፡፡ በማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ መልእክት ያስተላለፉት የምክክር ኮሚሽኑ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ኮሚሽኑ በአራት ካደራጃቸው የሥራ ምዕራፎች ውስጥ ሁለቱ መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል፡፡ ለሦስተኛው የምክክር ምዕራፍም በዝግጅት ላይ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ በምክክር ሂደቱ የሚሳተፉ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ የሃሳብ እና የፖለቲካ መሪዎች እንዲኾኑ በግልጽ መደንገጉንም ተናግረዋል፡፡
ኮሚሽኑ ተሳታፊዎችን የመለየት ሥራውን አሳታፊ እና አካታች ለማድረግ በጥንቃቄ ሲያከናውን መቆቱን ፕሮፌሰሩ አመላክተዋል፡፡ የአጀንዳዎች ልየታም ዛሬ መጀመሩንም ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ በሚደረገው ሀገራዊ ጉባኤ ምክክር የሚደረግባቸውን መሠረታዊ ጉዳዮችን አሳታፊ እና አካታች በኾነ መንገድ የመለየቱ ሥራ በራሱ ምክክር እና መግባባትን እንደሚጠይቅም ገልጸዋል፡፡
አጀንዳ ማሰባሰቡ ለቀጣዩ የምክክር ጉባኤ ስኬታማነት ቁልፍ ሚና እንደሚኖረውም አስታውቀዋል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደጉ የመጡ የሀሳብ ልዩነቶች ሀገራችንን ከልቀት ወደ ድቀት፣ ከፍቅር ወደ ጥላቻ፣ ከአንድነት ወደ መነጣጠል፣ ከሰላም ወደ ጦርነት እየጎተቷት በመሆኑ ምክንያቶችን ነቅሶ በመለየት ሰክኖና ተረጋግቶ፣ በመከባበር ወደ መግባባት መድረስ ብቸኛ መፍትሔ መኾኑን መገንዘብ ይገባል ብለዋል፡፡
ፕሮፌሰር መስፍን አዲስ አበባ ከተማችን ብቻ ሳትኾን ትንሿ ሀገራችንም ናት፤ ከየማዕዘኑ ለመጣን ሕዝቦች በጋራ ተከባብረን እና ተሳስበን የምንኖርባት፣ በእኩልነት የምንታይባት የአፍሪካ ርእሰ ከተማ ናት ብለዋል፡፡ምክክር ምን መልካም ነገር እንደሚያመጣ ለጎረቤት ሀገራት እና አህጉራችን አፍሪካ ለማሳየት የተዘጋጀንበት ወቅት ላይ ደርሰናልም ብለዋል፡፡
በሚገባ የሚተዋወቁ ሕዝቦች ይከባበራሉ፣ ይተሳሳበሉ፣ እርስ በእርሳቸው በእኩልነት ይተያያሉ፣ በሀገራቸውም እኩል ይኾናሉ ያሉት ፕሮፌሰሩ ማንኛውም ችግር የሚፈታው በሀሳብ ልዕልና መኾኑን ተረድቶ ከጉልበት መፍትሔ ይልቅ ሁሉንም አሸናፊ በሚያደርገው በምክክር መርህ መያዝ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
አዲስ ውጤት ለማግኘት በአዲስ መንገድ መሄድ አስፈላጊ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ ሕዝቡ በተወካዮቹ አማካኝነት ትርጉም ያለው ተሳትፎ ለማድረግ የሚሳትፍበት ታሪካዊ መድረክ መፈጠሩንም ተናግረዋል፡፡ ይሄን ታላቅና ታሪካዊ ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል መተማመን የሰፈነበት አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት ለመፍጠር ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ውስጣዊ ችግሮችን የሚፈታ የፖለቲካ ባሕል ለማዳበር ያስችላል ነው ያሉት፡፡
ወቅታዊ ችግሮችን ዘላቂ በመኾነ መንገድ ለመፍታት ሰላምን አስተማማኝ በኾነ መሠረት ለማቆም፣ ጠንካራና ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግሥት ለመገንባት፤ የሚደረገው ምክክር በስኬት እንዲቋጭ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ ፕሮፌሰር መስፍን አሳስበዋል፡፡ በምክክሩ ለሚለዩ አጀንዳዎች ተገቢውን ዋጋ በመስጠት፣ በቀጣይ በሚከናወነው የአጀንዳ ቀረጻ ተግባር ትኩረት ማድረግ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል፡፡ በአዲስ አበባ የተጀመረው አጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ እስከ ግንቦት 23 2016 ዓ.ም እንደሚቀጥልም አመላክተዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!