
ባሕር ዳር: ግንቦት 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ አባላት ከማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት መሪዎች እና ከሰሜን ሸዋ ዞን የሥራ ኀላፊዎች ጋር ውይይት አካሂደዋል። በውይይቱም በአካባቢው የሚታየው አሁናዊ የሰላም እና የጸጥታ ሁኔታ፣ በሰላም መደፍረስ ሂደት የተያዙ ተጠርጣሪዎች አያያዝ እና መረጃ አጣርቶ ለፍርድ የማቅረብ እንዲሁም የሰብዓዊ አያያዝ ሁኔታ በተመለከተ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተነጋግረዋል።
በአካባቢው ማንኛውም አካል ያለውን ፍላጎት እና ልዩነት ወደ ጠረጴዛ በማምጣት ተነጋግሮ በመፍታት፤ ለኅብረተሰቡ ዘላቂ የኾነ ሰላም ማረጋገጥ እንደሚገባ የቦርዱ አባላት ገልጸዋል። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተጠርጥረው የተያዙ ተጠርጣሪዎች መረጃቸውን የማጣራት ሥራ ተካሂዶ እንደየወንጀሉ ክብደት እና ቅለት ከተሃድሶ ሥልጠና እስከ ፍርድ ቤት የማቅረብ ሥራ እየተሠራ እንዳለ የዞኑ ኀላፊዎች ለቦርዱ አባላት ገለጻ አድርገዋል።
በዞኑ የሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች ያለው የሰላም ሁኔታ እየተሻሻለ መምጣቱን ተከትሎ የተለያዩ መደበኛ የልማት ሥራዎችን እያከናወኑ እንደሚገኙም ተናግረዋል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንደገለጸው በኮማንድ ፖስት ስር በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች ዘላቂ ሰላም እና ጸጥታን ከማረጋገጥ አኳያ ከአካባቢው የኅብረተሰብ ክፍል የተውጣጡ ወጣቶችን አደራጅቶ ሥልጠና እንዲያገኙ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!