
የአስፓልት መንገድ፣ የመገጭ መስኖ ግድብ እና የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የተሠጠውን አቅጣጫ ተግባራዊ ለማድረግ የክልሉ መንግሥት የክትትልና ድጋፍ ግብረ-ኀይል በማቋቋም ወደ ሥራ መግባቱ ተመላክቷል።
በክልሉ የተቋቋመው ግብረ ኀይልም ከፌደራል የፕሮጀክቶች አሠሪ ሚኒስተር መስሪያ ቤቶች ጋር በውኃና ኢነርጅ ሚኒስትር ቢሮ ውይይት አድርጓል። የ3ቱን ፕሮጀክቶች የሥራ እንቅስቃሴ በመገምገም ሚኒስትር መስሪያ ቤቶቹ እንዴት ሊሠሩ እንዳቀዱ፣ ከክልሉ መንግሥት የሚፈልጉትን ድጋፍ እና የቀጣይ የግንኙነት አግባቦች ምን መሆን እንዳለባቸውም የውይይቱ አጀንዳዎች ናቸው።
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔና አቅጣጫ በመነሳት ሁሉም የፌደራል አሠሪ መስሪያ ቤቶች ለፕሮጀክቶቹ በፍጥነት ወደ ሥራ መግባት የሰጡት ትኩረት እና አጀማመራቸው መልካም ቢሆንም የካሳ ክፍያ፣ የዲዛይን ችግሮች፣ የግብዓት አቅርቦት፣ የሥራ ፍጥነት፣ ጥራት፣ ለሚያጋጥሙ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ መስጠት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ በሚቻልበት ጉዳይ በውይይቱ መግባባት ተችሏል።