
ባሕር ዳር: ግንቦት 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በወቅታዊ የክልሉ ጉዳዮች ማብራሪያ ሰጥተዋል። በማብራሪያቸውም በክልሉ ከሕግ ማስከበር ጎን ለጎን የልማት ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን አስታውቀዋል። የመጀመሪያው የትኩረት መስክ የግብርና ልማት ሥራ መኾኑን አብራርተዋል። ከባለፉት ዓመታት አኳያ ቀደም ብሎ የግብርና ግብዓት ለማቅረብ መሠራቱንም ተናግረዋል። በብዛት፣ በወቅቱ በማድረስ እና በዋጋ ከባለፉት ዓመታት አንጻር የተሻለ መኾኑንም ገልጸዋል።
መሠረታዊ የኾነ የአቅርቦት ችግር አይኖርብንም፣ ችግሩ ስርጭት ላይ ነው፣ ዋናው ግብ ደግሞ ለአርሶ አደሮች በተገቢው መንገድ ማድረስ ነው ብለዋል። የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች በተገቢው መንገድ ለማሠራጨት ችግር መኖሩንም ተናግረዋል። ችግሮችን ለመፍታት መሥራት ይገባልም ብለዋል። በቂ ምርጥ ዘር መሰባሰቡንም ገልጸዋል።
ኢንቨስትመንት ለመሳብ፣ የአገልግሎት ዘርፉን ለማነቃቃት ጥረት መደረጉንም አመላክተዋል። በክልሉ ሀገራዊ እና ክልላዊ የትምህርት ፈተናዎችን መስጠት የሚቻልባቸውን እና የማይቻልባቸውን አካባቢዎች ለይተን እየሠራን ነውም ብለዋል። ፈተናዎችን ለመስጠት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
በክልሉ ሙስናን እና ብልሹ አሠራርን ለመቀነስ ሥራ ሲሠራ መቆየቱን የተናገሩት ርእሰ መሥተዳድሩ ግጭቱን ተከትለው የተከሰቱ የሙስና እና ሕገ ወጥ ተግባራት መኖራቸውን ነው የተናገሩት። መሬትን በጅምላ የማስተላለፍ እና ተደራጅቶ ለመዝረፍ የሚደረግ ሙከራ እንደነበርም አንስተዋል። ከመሬት ጋር የተያያዘውን ችግር ለማስተካከል የመፍትሔ ርምጃዎች መወሰዳቸውን ተናግረዋል። ከመሬት ጋር በተያያዘ ሕገ ወጥ ተግባር የፈጸሙ አካላትን በሕግ ጥላ ሥር አውለናል ነው ያሉት።
በሕገ ወጥ ተግባር ላይ የተሠማሩ አካላትን በተገቢው መንገድ ለመታገል እየሠራን ነው ብለዋል። የክልሉን ወቅታዊ ችግር ተጠቅሞ ለግል ጥቅሙ በሕገወጥ ተግባር ላይ የሚሠማራን አካል አምርረን መታገል አለብን ነው ያሉት። ርእሰ መሥተዳድሩ ከኢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ የክልሉ የሰላም ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ በመኾኑ ሕግወጥ ተግባራትን ለመቆጣጠር እድል እንደሚሰጥም አመላክተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!