በበጀት ዓመቱ ከ15 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፈጠሩን የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ገለጸ።

16

እንጅባራ: ግንቦት 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር በ2016 በጀት ዓመት ከ71ሺህ በላይ ለሚኾኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ባለፉት 10 ወራት 15 ሺህ 625 የሥራ ዕድል መፈጠሩ ተገልጿል፡፡ ብሔረሰብ አሥተዳደሩ ወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ ሰፊ ጸጋዎች ቢኖሩትም ባለፉት ወራት በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ መደፍረስ ተግባራትን በታቀደው ልክ ለመፈፀም እንዳላስቻላቸው የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሥራ እና ሥልጠና መምሪያ ኀላፊ ታፈረ ከበደ ተናግረዋል።

የተፈጠረው የሰላም እጦት በርካታ ኢንተርፕራይዞችን እና ኮሌጆችን ከሥራ ውጭ በማድረግ በሥራ ፈላጊዎች ላይ ጫና መፍጠሩንም ነው አቶ ታፈረ ያነሱት ። በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ባለፉት 10 ወራት የተፈጠረውን ጫና በመቋቋም ከ15 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው የገለጹት ኀላፊው ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ የመሥሪያ ብድር እና ከ200 ሄክታር በላይ የማምረቻ እና መሸጫ መሬት እንደተመቻቸላቸውም ተናግረዋል።

የሰላም ሁኔታው መሻሻል በታየባቸው ወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳደሮች በቀሪ ወራት ወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተገልጿል።

ዘጋቢ፡- ሳሙኤል አማረ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት የተገነባው አዳሪ ትምህርት ቤት የዜጎችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ አብነት የሚኾን የልማት ሥራ ነው” ወርቀሰሙ ማሞ
Next articleበክልሉ ከሕግ ማስከበር ጎን ለጎን የልማት ሥራዎች በትኩረት እየተሠሩ መኾናቸውን ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ ገለጹ።