“በቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት የተገነባው አዳሪ ትምህርት ቤት የዜጎችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ አብነት የሚኾን የልማት ሥራ ነው” ወርቀሰሙ ማሞ

24

ባሕር ዳር: ግንቦት 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሼይካ ፋጢማ ቢንት ሙባረክ የዐይነ ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት የዜጎችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ አብነት የሚኾን የልማት ሥራ መኾኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባሕል እና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ ወርቀሰሙ ማሞ ገልጸዋል።

በቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት የተገነባው የሼይካ ፋጢማ ቢንት ሙባረክ የዐይነ ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት ባሳለፍነው ሳምንት መመረቁ ይታወሳል። ትምህርት ቤቱ በ41 ሺህ 300 ካሬ ሜትር ያረፈ እና ግንባታው ሁለት ዓመት የፈጀ ሲኾን 15 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጎበታል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባሕል እና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ ወርቀሰሙ ማሞ እንደተናገሩት በቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች በርካታ አቅመ ደካማ ወገኖችን ተጠቃሚ ያደረጉ ናቸው፡፡ በቅርቡ የተገነባው የሼይካ ፋጢማ ቢንት ሙባረክ የዐይነ ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት ዐይነ ስውራን ዕውቀት እና ክህሎታቸውን ለሀገር ልማት እንዲያውሉ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መኾኑን ተናግረዋል።

ይህም በተለይ በማኅበራዊ ዘርፍ የዜጎችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ አብነት የሚኾን ሥራ ስለመኾኑም ተናግረዋል፡፡ ከቀዳማዊ እመቤት ጽሕፈት ቤት ልምድ በመውሰድ በየአካባቢው የዜጎችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ሥራዎች እንዲሰፉ ሁሉም የበኩሉን ሚና እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ኢዜአ እንደዘገበው አካል ጉዳተኞች ዕውቀት እና ክህሎታቸውን ለሀገር ልማት እንዲያውሉ ምቹ ሁኔታዎች መፍጠር ላይ በትብብር መሥራት አንደሚገባም ነው ያነሱት፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article”ለጠንካራ የጤና ሥርዓት ግንባታ ጠንካራ የጤና አመራር ሥርዓት አስፈላጊ ነው” የአማራ ክልል ጤና ቢሮ
Next articleበበጀት ዓመቱ ከ15 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፈጠሩን የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ገለጸ።