
ባሕር ዳር: ግንቦት 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የጤና ኢኖቬሽን መመሪያ፣ ውጤታማ የጤና አመራር አሥተዳደር እና ተጠያቂነት፣ የጤና ተቋማት አክሪዲቴሽን ፍኖተ ካርታ እና በመጀመሪያ አሃድ ጤና ተቋማት የሥርዓት ማነቆ ላይ ያተኮረ ፊፎረም በይፋ አስጀምሯል።
በፕሮግራሙ የጤና ዘርፍ አመራሩን እና አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል በተሠሩ እና በቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ውይይት ተደርጓል።
የደቡብ ወሎ ዞን ጤና መምሪያ የህክምና አገልግሎት አስተባባሪ ሀዋ ኢብራሂም በየደረጃው ባለ የጤና አመራር ላይ በሚሠራው አቅም ግንባታ ብዙ መሻሻሎች እንደሚኖሩ አምናለሁ ብለዋል። አመራሩ በዕውቀት ተመስርቶ እንዲመራ ሥልጠና መሰጠቱ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን እንደሚያሻሽለው ገልጸዋል።
የደብረ ብርሃን ሆስፒታል ጠቅላላ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሥራ አሥኪያጅ አስማረ ሳሙኤል ሥልጠናው በሆስፒታሎች የሚያጋጥሙ ችግሮችን ፈትቶ የሕዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ የጤና አመራሩን አቅም የመገንባት አስፈላጊነት፣ በጤናው ዘርፍ ያሉ ማነቆዎችን ለይቶ እና ዕድሎችን ተጠቅሞ በመፍታት ቀልጣፋ አገልግሎት የሚሰጥበት እና የጤና ተቋማት በተቀመጠው የአገልግሎት አሰጣጥ ደረጃን በመተግበር እውን የሚደረግበትን ስልት ተወያይተናል ብለዋል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ ጠንካራ የጤና ሥርዓት ለመገንባት ጠንካራ የጤና አመራር ሥርዓት አንዱ መኾኑን ገልጸዋል። ይህንን ለመፍጠርም የውጤታማ አመራር አሥተዳደር እና ተጠያቂነት ሥርዓትን ለማስፈን በጤናው ዘርፍ የአሥተዳደር ተግባራትን ለመፍጠር እንዲሁም በመጀመሪያ ደረጃ ጤና አገልግሎቶች ያሉ ጉድለቶች እና መፍትሔ ለመውሰድ ውይይት መደረጉን ጠቅሰዋል።
አመራሩ በሰፊው አቅዶ እንዲሠራ፣ ማኅበረሰቡን በማነቃነቅ ለውጤት በማብቃት እና የሠራተኞችን ክፍተት እና ጠንካራ ጎን ለይቶ የበለጠ የሚያሠራ እንዲኾን አመራር የመፍጠር ዓላማ ተይዞ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። አሁን ያለውን ነባራዊ ኹኔታ ሊቋቋም የሚችል የጤና አመራር እና ሙያተኛ እንዲሁም ማኅበረሰብ እንደሚያስፈልግ የጠቀሱት ኀላፊው የጤና ችግሮችን አውቀን በጋራ ለመሥራት ነው ውይይቱ የተደረገው ብለዋል።
በጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ በጤናው ዘርፍ የኅብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ ብዙ ሥራ መሠራቱን እና ስኬቶችም መገኘታቸውን ገልጸዋል። አሁን ላይ ዘርፉ የሚፈተንበት ጊዜ መኾኑንም ጠቅሰዋል። በጤናው ዘርፍ ለተደራሽነት ብዙ ቢሠራም ሥርዓቱን ጠንካራ በማድረግ እና ውስን ሃብትን በአግባቡ በመጠቀም በኩል ውስንነቶች መኖራቸውን ገልጸዋል። ይህንን ለማሻሻልም ሥራ መጀመሩን ጠቅሰዋል።
20 በመቶ የሚኾን የሃብት እና ውጤት አለመመጣጠን የማኅበረሰቡ የባለቤትነት ፍላጎት ማደግ እንዲሁም የደራሽ ሥራዎች መብዛት የጤና ሥርዓቱን ለማጠናከር አስገዳጅ ሁኔታዎችን ተናግረዋል። የጤና ሥርዓቱ የሚገመት እና የሚለካ እንዲኾን በቴክኖሎጂ ደግፎ ማሻሻል፣ የፈጠራ ሥራዎችንም ማጠናከር፣ የደኅንነት፣ ፍትሐዊነት እና የቁጠባ አሠራሮችን በማዳበር የትብብር ሥራ እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል።
ከባሕላዊ የአመራር ሥርዓት ወጥተን በጤና ሥርዓቱ የተቃኘ ውጤታማ አመራር ለመፍጠር እና ለመገንባት ከማሻሻያው እስከ ተጠያቂነቱ ድረስ ፕሮግራም ተቀርጾ ወደ ሥራ ገብተናል ያሉት ዶክተር አየለ ያለውን ሃብት ለበለጠ ውጤት ለማድረስ በፈጠራ እና በለውጥ ሃሳቦችን መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል።
መዳረሻ ለኾነው ሁለንተናዊ የጤና ሽፋን የተበታተኑ አሠራሮች አቀናጅቶ መምራት ግዴታ እንደኾነ ገልጸዋል። አጠቃላይ አገልግሎት እና የልህቀት ማዕከልነትንም አጣምሮ መሥራት በጤናው ዘርፍ ተፈላጊ ነው ብለዋል። በዘርፉ ኅብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲኾንም ያለ ቅድመ ሁኔታ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!