
ባሕር ዳር: ግንቦት 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በበጀት ዓመቱ 10 ወራት 3 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ መቻሉን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ሃና አርያስላሴ ገልጸዋል። ኮሚሽነሯ መንግሥት ኢትዮጵያን ምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሢሰራ ቆይቷል ነው ያሉት፡፡
አዳዲስ ሴክተሮችን፣ የወጪ እና ገቢ ንግድ እንዲሁም ከዚህ ቀደም ዝግ የነበሩ ሴክተሮች ለኢንቨስትመንት ክፍት ማድረግ ደግሞ ከተወሰዱ የማሻሻያ እርምጃዎች መካከል መኾናቸውን ጠቅሰዋል። በኢትዮጵያ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች ለውጭ ባለሃብቶች የሚያስተዋውቁ መረሐ-ግብሮችን በማስተዋወቅ ረገድ ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በግብርና፣ በማምረቻ፣ በኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ፣ በቱሪዝም፣ በጤና እንዲሁም በሌሎችም ዘርፎች ላይ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው መዋዕለ ነዋያቸውን ለሚያፈሱ ባለሃብቶች የምትሰጠውን ማበረታቻ እያስተዋወቀች ትገኛለች ብለዋል። ባለፉት ዓመታት የፋይናንስ ዘርፉ ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎች ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ምቹ ሁኔታ እየፈጠሩ መኾናቸውንም አብራርተዋል፡፡
በ2016 በጀት ዓመት ኮሚሽኑ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ዕቅድ ይዞ ሢሠራ መቆየቱን ጠቅሰዋል፡፡ በዚህም በበጀት ዓመቱ 10 ወራት 3 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መሳብ ተችሏል ነው ያሉት፡፡ ቻይና፣ ኔዘርላንድ፣ ቱርክ እና ሕንድ ደግሞ በኢትዮጵያ በውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ከሚሳተፉ ዋና ዋና ሀገራት መካከል መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡ በተለይ የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መዋለ ንዋያቸውን በማፍሰስ ቀዳሚውን ደረጃ እንደሚይዙ መጥቀሳቸውን የኢዜአ መረጃ ያሳያል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!