የኢትዮጵያን የልማት እንቅስቃሴዎች ለመደገፍ ቁርጠኛ መኾናቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ረዳት ዋና ጸሐፊ ራሚዝ አላክባሮቭ (ዶ.ር) ገለጹ፡፡

26

ባሕር ዳር: ግንቦት 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ ተቀማጭነታቸው በአዲስ አበባ ካደረጉት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ረዳት ዋና ጸሐፊ እና የሰብዓዊ እርዳታ አስተባባሪ ራሚዝ አላክባሮቭ (ዶ.ር) ጋር በጽሕፈት ቤታቸው ውይይት አድርገዋል።
ሚኒስትሩ እና ረዳት ዋና ጸሐፊው የመንግሥታቱ ድርጅት ለሀገራዊ ልማት ዕቅዶች የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲያሳድግ በሚያስችሉ ማሻሻያዎች ዙሪያ ሀሳብ ተለዋውጠዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን አጋርነት እና ትብብር የበለጠ በማጠናከር ሀገራዊ የልማት ጥረቶችን መደገፍ እና ለሰብዓዊ ሁኔታዎች ምላሽ መስጠት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይም ገንቢ ውይይት አድርገዋል። ሀገራዊ የትኩረት መስኮችን እና ትልሞችን እውን ለማድረግ ቅንጅትን እና ውጤታማነትን ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይም ሀሳብ ተለዋውጠዋል።

ሚኒስትሩ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ወሳኝ የልማት አጋር እንዲኾን እና ለአባል ሀገራቱ ውጤታማ ድጋፍ ማድረግ እንዲችል የተቋሙን አሠራሮች እና ትኩረቶች ማሻሻል አስፈላጊ መኾኑን ነው የገለጹላቸው። አምባሳደር ታዬ ዶክተር ራሚዝ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ መንግሥት ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው አረጋግጠውላቸዋል። ዶክተር ራሚዝ ጽሕፈት ቤታቸው የኢትዮጵያን የልማት እንቅስቃሴዎች ለመደገፍ ያለውን ቁርጠኝነት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ኢትዮጵያን ወደ ነበረችበት እድገት ይመልሳል” የሕግ ባለሙያ
Next article“3 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ ተችሏል” የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን