
ባሕር ዳር: ግንቦት 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲን ካጸደቀ ከአንድ ወር በላይ አስቆጥሯል። ፖሊሲውን ለማርቀቅም በፍትሕ ሚኒስቴር የተቋቋመ የሕግ ባለሙያዎች ቡድን ከዓመት በላይ ጥናት እና ግምገማ ማካሄዱን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር ፍትሕ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ እና የሕግ አማካሪው ደሳለኝ ዘማርያም የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ከባድ ወንጀሎችን፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ አካባቢያዊ አለመግባባቶችን እና መሰል ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት የሚያሥችል ረቂቅ ፖሊሲ መኾኑን ይገልጻሉ። የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ዘላቂ ሰላምን ማስፈን እና የተናበበ የሽግግር ፍትሕ ሂደትን ለመዘርጋት ዓላማ እንዳለው የጠቀሱት አቶ ደሳለኝ ይህ ፖሊሲ የኢትዮጵያን የሰላም እጦት በዘላቂነት ሊፈታ የሚችል ነው ብለዋል።
የሽግግር ፍትሕ የወንጀል ተጠያቂነትን፤ እውነትን ማፈላለግ፣ ይፋ ማውጣት እና የዕርቅ ተግባር፤ የምህረት፤ ማካካሻ፤ ተቋማዊ ማሻሻያ፤ ፖሊሲው ተግባራዊ የሚደረግበት የጊዜ ወሰን የተመለከቱ አንኳር የሽግግር ፍትሕ ስልቶችን ያቀፈ ነው፡፡ በመኾኑም በሀገሪቱ ያሉ ወንጀለኞችን በሕግ ለመዳኘት የሚያስችል እንደኾነም ጠቁመዋል። በተለይም በአማራ ክልል ያለውን የሰላም መደፍረስ በሰላም ለመቋጨት የክልሉ ሕዝብ ከሰላም እና ከሕግ ጎን ሊቆም እንደሚገባ አሳስበዋል።
ዘጋቢ፡- ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!