
ደሴ: ግንቦት 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ የበጀት ዝግጅት እና አሥተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር፣ የፕላን እና ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ እና በክልሉ ምክር ቤት የሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ አሚኮ በደሴ ከተማ እያስገነባ የሚገኘውን የሚዲያ ኮምፕሌክስ ግንባታ ሂደት ተመልክተዋል።
አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ከ540 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በመመደብ ባለ 14 ወለል የሚዲያ ኮምፕሌክስ በደሴ ከተማ እያስገነባ ይገኛል። ግንባታው ከሁለት ዓመት በፊት የተጀመረው እና በአማራ ሕንፃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ተቋራጭነት እና በአማራ ዲዛይን ቁጥጥር አማካሪነት እየተገነባ የሚገኘውን ሕንፃ በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ ያለእረፍት እየተሠራ እንደሚገኝ የፕሮጀክቱ ተቆጣጣሪ መሀንዲስ አድነው አያሌው ተናግረዋል። አሁን ላይ የግንባታው ሂደት ከ30 በመቶ ማለፉንም ገልጸዋል።
በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ለኮርፖሬት አገልግልግሎት ምክትል ሥራ አሥፈጻሚ አስቻለ አየሁዓለም አሚኮ በሚዲያው ዘርፍ ተደራሽነቱን ለማስፋት እና የምሥራቅ አማራ የሚዲያ ማዕከል እንዲኾን በማሰብ በደሴ ከተማ ባለ 14 ወለል የሚዲያ ኮምፕሌክስ እያስገነባ ይገኛል ብለዋል። ከ540 ሚሊዮን ብር በላይ የተበጀለት የሕንፃ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ተቋራጩ እያደረገ ባለው ጥረት ደስተኛ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ፕላን እና ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ጥላሁን ወርቅነህ እና በክልሉ ምክርቤት የሴቶች ሕፃናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ እመቤት ከበደ አሚኮ በደሴ ከተማ እያስገነባ የሚገኘው ሕንፃ የግንባታ ሂደት በጥሩ አፈፃፀም ላይ እንደሚገኝ መመልከታቸውን ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ የበጀት ዝግጅት እና አሥተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሙሉሰው አይቼው በክልሉ በሰላም እጦት በርካታ የግንባታ ፕሮጀክቶች መቆማቸውን ገልጸዋል፡፡ “አሚኮ በደሴ ከተማ እያስገነባ የሚገኘው የሚዲያ ኮምፕሌክስ ግን በጥሩ ሂደት ላይ እንደሚገኝ ተመልክቻለሁ” ብለዋል።
የሕንጻው የግንባታ ሂደት ለሌሎች ፕሮጀክቶች ትምህርት የሚሰጥ እና ተሞክሮ የሚቀመርበት መኾኑም ተገልጿል። ግንባታው ሲጠናቀቅ ለአሚኮ ተደራሽነት እና ዘመናዊ የሚዲያ አሠራር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በደሴ ከተማ እያስገነባ የሚገኘው የሚዲያ ኮምፕሌክስ ሦስት የቴሌቪዥን ስቱዲዮ፣ ሦስት የሬዲዮ ስቱዲዮ፣ ቢሮዎች፣ ከ30 በላይ ተሽከርካሪዎችን የሚያስተናግድ እና ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የኤሌክትሪክ ቻርጅ ማድረጊያ የሚገጠምለት ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ፣ ሬስቶራንት እና የሥብሠባ አዳራሽ ያካተተ ነው፡፡ በሦስት ዓመት ተኩል ለማጠናቀቅ እየተሠራ ይገኛል።
ዘጋቢ፡- ከድር አሊ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!