
አዲስ አበባ: ግንቦት 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሁለተኛው ቢግ አምስት ኮንስትራክት ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የግንባታ አውደ ርዕይ ከግንቦት 22 እስከ 24/2016 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ ይካሄዳል። የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ዮናስ አያሌው ለሶስት ቀናት የሚቆየው ይህ የኮንስትራክት ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ትርዒት በሀገራችን በግንባታ ኢንዱስትሪው ረገድ ላለው እድገት ትልቅ ፋይዳ ያለው መኾኑን ገልጸዋል፡፡
በተለይም የዓለም አቀፍ ተቋማትን ተሞክሮ በመውሰድ እና ወደ ተግባር በመቀየር ረገድ ያለው ፋይዳ የጎላ መኾኑን ኢንጅነሩ ተናግረዋል። የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ ዝግጅቱ የኢንዱስትሪ መሪዎችን አንድ በማድረግ በኢትዮጵያ የግንባታ ዘርፉን ከፍ ማድረግን መሰረት ያደረገ ነው ብለዋል፡፡ በተለይ የሀገራችንን የግንባታ ዘርፍ እድገት እና ለውጥ እንዲሁም እድሎችን በማሳየት ተሳታፊዎች እንዲገነዘቡ በማድረግ እና ልምድ በመቅሰም ረገድ ትርዒቱ ሰፊ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።
ዘርፉ በአዳዲስ እሳቤ እና እይታዎች የታገዙ ሥራዎች የሚቀርቡበት፣ በተለይም ለሀገራችን ይዞት የሚመጣው ጥቅም የተሻለ በመኾኑ ትርዒቱ ትልቅ እድል ያለው መኾኑ ተጠቅሷል። ቢግ አምስት ኮንስትራክት ኢትዮጵያ ትልቁ እና ዓለም አቀፋዊ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ክስተት በመኾኑ በሀገሪቱ የኮንስትራክሽን ዘርፍ አዳዲስ እና ነባር ፕሮጀክቶች ላይ ለመሰማራት አዳዲስ የቢዝነስ እድሎችን የሚፈትሹ አቅራቢዎችን ያገናኛል። ኅብረተሰቡም በዚህ ዓለም አቀፋዊ ኹነት በመታደም እና በመጎብኘት ለሀገራችን ብሎም ለዘርፉ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ ጥሪ አቅርበዋል።
በቢግ አምስት ኮንስትራክት ኢትዮጵያ ከ26 የዓለም ሀገራት የተውጣጡ 160 አውደ ርዕዮች፣ 20 ነጻ ሲዲፒ የተመሰከረላቸው ዓለም አቀፍ የሥራው ባሙያዎች የዲዛይን እና ግንባታ እንዲሁም የሕንፃ ጥገና እና ፋሲሊቲ አሥተዳደር ባለሙያዎችን ጨምሮ ተደማጭነት ያላቸው የኢንዱስትሪ ውሳኔ ሰጪዎች፣ ባለሙያዎችም ይሳተፋሉ። ዝግጅቱን የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን በጋራ እንደሚያዘጋጁት ተነግሯል።
ዘጋቢ፡- ሠለሞን አሰፌ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!