ኮሚሽኑ በደብረ ብርሃን ክላስተር ሲያካሂድ የነበረውን የተባባሪ አካላት ሥልጠና አጠናቀቀ፡፡

11

ባሕር ዳር: ግንቦት 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከሰሜን ሸዋ ዞን ከ31 ወረዳዎች እና ከአምስት ክፍለ ከተሞች ለተወከሉ 282 ተባባሪ አካላት ከግንቦት 14 እስከ 16/2016 ዓ.ም ድረስ በደብረ ብርሃን ከተማ ሥልጠና ሰጥቷል። በሥልጠናው የሀገራዊ ምክክር ጽንሰ ሀሳቦች፣ የአጀንዳ ማሰባሰብ፣ የተሳታፊዎች አመራረጥ ሥርዓት እና የተባባሪ አካላትን ሚና በተመለከተ ሰነዶች ቀርበው ገለጻ እና ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በሥልጠናው የተሳተፉ ተባባሪ አካላት ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የሁሉንም ማኅበረሰብ አጀንዳዎች ለማካተት እያከናወነ ያለውን ተግባር አድንቀዋል፡፡ ወኪሎች በተሰጣቸው መመሪያ መሠረት በታማኝነት ሥራውን እንደሚያከናውኑ ገልጸዋል፡፡ ተባባሪ አካላቱ በየወረዳቸው በመሄድ በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት የሚሳተፉ ወኪሎችን ከአሥር የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ያስመርጣሉ፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአሥር ክልሎች እና በሁለት ከተማ አሥተዳደሮች የአጀንዳ ማሰባሰብ ወኪሎችን አስመርጦ የጨረሰ ሲኾን፤ በአማራ ክልል ባለፉት ሁለት ሳምንታት በተለያዩ ከተሞች የተባባሪ አካላት ሥልጠና አከናውኗል፡፡ ኮሚሽኑ የምክክር ምዕራፉን በመጪው ረቡዕ ግንቦት 21/2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ደረጃ እንደሚጀምር የኢትዮጵያ የምክክር ኮሚሽን የትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ሰነድ የትግበራ ምዕራፍ የፍኖተ ካርታ ዝግጅት ሥራ እየተሠራ መኾኑን ፍትሕ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
Next articleየአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ወጣቶች የሀገር ዋልታና መከታ የኾነውን መከላከያ ሠራዊት እየተቀላቀሉ ነው።