የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ሰነድ የትግበራ ምዕራፍ የፍኖተ ካርታ ዝግጅት ሥራ እየተሠራ መኾኑን ፍትሕ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

16

ባሕር ዳር: ግንቦት 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በፍትሕ ሚኒስቴር የብሔራዊ ሰብዓዊ መብቶች ድርጊት መርሐ ግብር ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አወል ሱልጣን እንደገለጹት በሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ሰነዱ የተመላከቱ ስልቶች ቅደም ተከተላቸውን ጠብቀው እንዲተገበሩ ወደሚያስቻለው የፍኖተ ካርታ ዝግጅት ሥራ ተሸጋግሯል፡፡ በዚህም ባለፈው ሳምንት የተጀመረውን ተግባር በቀሪዎቹ ሁለት ሳምንታት ለማጠናቀቅ እየተሠራ ይገኛል፡፡

ፍኖተ ካርታው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ የትግበራ ምዕራፍ ምን ላይ ተጀምሮ ምን ላይ እንደሚያበቃ የሚያመለክት እና በሂደቱ የሚከናወኑ ተግባራትን የሚዘረዝር መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ተግባራቱን የሚያከናውኑ ተቋማት የትግበራ ምዕራፉ የሚጠናቀቅበት ጊዜ እና አስፈላጊ በጀትንም በአግባቡ የሚያመላክት ነውም ብለዋል፡፡

ፍኖተ ካርታው በመንግሥት ተቋም ባለሙያዎች ብቻ የሚሠራ ሳይኾን ከሲቪክ ማኅበረሰብ ተወካዮች እና ከሰብዓዊ መብት ድርጅቶች የተውጣጡ ባለሙያዎች የሚሳተፉበት መኾኑንም ነው የጠቆሙት፡፡ ተጠያቂነትን ማስፈን፣ ቅድመ ሁኔታን ከግምት ያስገባ ምህረት፣ እውነትን ማፈላለግ እና ይፋ ማድረግ፣ ይቅርታ፣ የማካካሻ እና የተቋም ግንባታ ሥራዎች በሰነዱ መካተታቸውንም አመልክተዋል፡፡

ስልቶቹን የሚያስተገብሩ ገለልተኛ ተቋማት እንዲዋቀሩ በፖሊሲው መመላከቱንም አስታውሰዋል። ተቋማቱ ከተቋቋሙ በኋላ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲውን ማስተግበር የቀጣይ ትግበራ አካል ይኾናል ነው ያሉት፡፡ በገለልተኛነት የሚቋቋሙ የእውነት ማፈላለግ ኮሚሽን፣ የተቋም ግንባታ ኮሚሽን፣ ልዩ ዐቃቤ ሕግ እና ልዩ ችሎት በፖሊሲው የተመላከቱትን ስልቶች ያስተገብራሉ፡፡ ፍትሕ ሚኒስቴር ተቋማቱን ለማቋቋም የሚያስችሉ ሥራዎች የሲቪል ማኅበረሰብ እና የሰብዓዊ መብት ድርጅቶችን በማስተባበር እየሠራ መኾኑን አመልክተዋል፡፡

ስልቶቹን ለማስተግበርም የሕግ ማእቀፎች ይወጣሉ፣ ማኅበረሰቡ ግንዛቤው ኖሮት በባለቤትነት ስሜት እንዲሳተፍ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ጎን ለጎን ይሠራሉ፡፡ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ከዚህ በፊት ከነበሩ ፖሊሲዎች እና የሕግ ማዕቀፎች በተለየ መልኩ የሕዝብ ባለቤትነት የሚያስፈልግ መኾኑን ግምት ውስጥ በማስገባት ከጅምሩ ሕዝብ በማሳተፍ ግብዓት ሊኾኑ የሚችሉ የተለያዩ አማራጮችን የያዘ የፖሊሲ አማራጮችን የያዘ ሰነድ ተዘጋጅቶ ለሕዝብ እንዲሰራጭ መደረጉንም አመልክተዋል፡፡

በሰነዱ ላይ ተመርኩዞ ማንኛውም ሰው በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች አንብቦ መካተት ስለሚገባቸው ጉዳዮችም አስተያየት እንዲሰጥበት መደረጉን አውስተዋል፡፡ በአዲስ አበባ ስድስት የውይይት መድረኮች በማካሄድ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የግብዓት ማሠባሠብ ሥራ መከናወኑንም ተናግረዋል፡፡

በተለያዩ ክልሎች በመንቀሳቀስ የቀጠለው ተግባርም ከ49 በላይ መድረኮች የግብዓት ማሠባሠብ ሥራ የተካሄደበት እንደነበር ገልጸዋል፡፡ በሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አማራጭ ሃሳቦች ላይ ሕዝቡ የሚሰማውን ሃሳብ እንዲያንጸባርቅ መደረጉን እና ያለተጽእኖ እንዲካሄድ ለማድረግም ከ200 በላይ የዩኒቨርሲቲ መምህራን እንዲሳተፉበት መደረጉንም አብራርተዋል፡፡

ከክልል ውጪ በኾኑ ጉዳዮች ደግሞ ተጎጂዎችን፣ ሕፃናትና ሴቶችን ተሳታፊ ያደረጉ ከ20 በላይ መድረኮች ለየብቻቸው መካሄዳቸውንም ነው የገለጹት፡፡ መድረኮቹ ሲካሄዱ 13 አባላት ያሉት ገለልተኛ የባለሙያዎች ቡድን ተደራጅቶ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ የፖሊሲ አማራጮቹ የተዘጋጁት፣ የምክክር መድረኩም የተመራው ገለልተኛ ከኾኑ ባለሙያዎች ማለትም ከጠበቆች፣ ከዩኒቨርሲቲዎች እና በየግላቸው ከሚሠሩ በጉዳዩ ላይ ረጅም ጊዜ የተመራመሩ ፣ ያጠኑ፣ ያሠለጠኑ፣ ያማከሩ እና ያስተማሩ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ቡድኑ ሥራውን ካጠናቀቀ በኋላ ረቂቅ የሽግግር ፖሊሲ ሰነዱን አስረክቧል፡፡

እንደ ኀላፊው ገለጻ ረቂቅ የሽግግር ፖሊሲ ሰነዱ ላይ አራት መድረኮች ተደርገዋል፡፡ የተገኘውን ግብዓት በማካተትም የመጨረሻውን የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ሰነድ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ማቅረብ ችሏል፡፡ ኢፕድ እንደዘገበው ምክር ቤቱም ለሀገር ሰላም መስፈን፣ ለእኩልነት፣ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ ለሕግ የበላይነት መስፈን ያለውን አስተዋጽኦ ግምት ውስጥ በማስገባት ለጉዳዩ ቅድሚያ በመስጠት በጉዳዩ ላይ መክሮ በአጭር ጊዜ ጸድቆ ወደ ተግባር አስገብቷል ብለዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ለመኸር እርሻ ቀድመን ተዘጋጅተናል” አርሶ አደሮች
Next articleኮሚሽኑ በደብረ ብርሃን ክላስተር ሲያካሂድ የነበረውን የተባባሪ አካላት ሥልጠና አጠናቀቀ፡፡