“ለመኸር እርሻ ቀድመን ተዘጋጅተናል” አርሶ አደሮች

49

ባሕር ዳር: ግንቦት 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በ2016/17 የመኸር እርሻ ከ5 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በማልማት ከ169 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት ታቅዷል፡፡ አርሶ አደር ውባለም ዋለልኝ የወገራ ወረዳ የጀጀህ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። አርሶ አደር ውባለም ስንዴ፣ የቢራ ገብስ፣ ነጭ ገብስ እና ሌሎችንም ሰብሎች ያመርታሉ። ስንዴ የሚዘሩትን ማሳቸውን ሦስት ጊዜ አርሰውታል፣ የአፈር እና የቅጠል ማዳበሪያ አዘጋጅተናል ነው ያሉት። ለመኸር እርሻው ቀድመው ተዘጋጅተዋል። ምርጥ ዘር እየተጠባበቁ ነው።

አርሶ አደር ውባለም ለእርሻ ሥራ መዘናጋት እንደማይገባ ተናግረዋል። “ገቢያችን ያደገ፣ ማዕዳችን የሞላ፣ ልጆቻችንን ያስተማርን፣ አትርፈን የሸጥን እርሻችንን በአግባቡ በማረሳችን እና ማዳበሪያ በመጠቀማችን ነው” ብለዋል። “አሁን ልማት ላይ ነን” በእርሻ አይቀለድም ነው ያሉት፡፡ ማዳበሪያ በበቂ መጠን እንድንጠቀም በመምከር በኩል የቀበሌ የግብርና ባለሙያዎች የሚያደርጉልን ድጋፍ የሚበረታታ ነው። በዚህ መቀጠል አለባቸው ብለዋል።

ከአምናው የተሻለ ምርት ለማምረት ያቀዱት አርሶ አደር ውባለም ሁሉም አርሶ አደር የእሳቸውን መርህ ሊከተል ይገባል ነው ያሉት። ሌላው አርሶ አደር አወቀ ተስፋ ወገራ ወረዳ ጀጀህ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። ስንዴን ጨምሮ የተለያዩ ሰብሎችን ያመርታሉ፡፡ ሁለት ሄክታር መሬት ደጋግመው በማረስ አለስልሰዋል። ወረዳ ላይ የቀረበውን ማዳበሪያም ገዝተው ወስደዋል። አንዱን ሄክታር መሬት የምግብ ገብስ እና ስንዴ ሊዘሩ ተዘጋጅተዋል፡፡

አርሶ አደር አወቀ ምርጥ ዘር እና ማዳበሪያ መጠቀም ሳይጀምሩ ደጋግመው ሳያርሱ ያገኙ የነበረ ሁለት ኩንታል ስንዴ ብቻ ነበር። አሁን የግብርናን ምክረ ሃሳብ በመቀበላቸው ምርታቸው ወደ 9 እና 10 ኩንታል አድጓል። ቀበሌያቸው ከዞኑ የራቀ መኾኑ ግብዓት በሚፈልጉት ሰዓት እንዳያገኙ ያደርጋቸው ነበር። አሁን መንግሥት ለሁሉም በሰጠው ትኩረት ወረዳ ላይ ግብዓት እያገኙ መኾኑንም ተናግረዋል። ደጋግመን በማረስ ለዘር ተዘጋጅተናል ነው ያሉት።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ ንጉሴ ማለደ የ2016/17 የመኸር እርሻን ውጤታማ ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ሥራው በንቅናቄ መጀመሩን ተናግረዋል። በዞኑ 529 ሺህ 570 ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን 17 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት ታቅዷል። በዋና ዋና ሰብሎች ላይ ምርታማነትን ለመጨመር ግብዓት በወቅቱ መጠቀም፣ ደጋግሞ ማረስ፣ ምርጥ ዘር መጠቀም፣ በመስመር መዝራት እና አረምን መከታተል ዋና ዋና ተግባራት መኾናቸውን ነው የጠቆሙት።

ለማዕከላዊ ጎንደር ዞን 580 ሺህ 350 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በክልል ደረጃ የተፈቀደ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ውስጥም 318 ሺህ 750 ኩንታል ወደ ዞኑ የገባ ሲኾን 172 ሺህ 362 ኩንታል ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች ተሰራጭቷል፡፡ ለዞኑ ከሚያስፈልገው 9 ሺህ 490 ኩንታል የበቆሎ ምርጥ ዘር 5 ሺህ 240 ኩንታል በላይ ወደ ዞኑ ገብቷል፡፡ ከዚህ ውስጥ 1 ሺህ 720 ኩንታል በላይ የበቆሎ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሮች ተሰራጭቷል ነው ያሉት፡፡

የአፈር ለምነትን ከመጠበቅ አንጻር 13 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማዘጋጀት የታቀደ ሲኾን 78 በመቶ ያህሉን በማዘጋጅት ወደ ማሳ የመበተን ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ኀላፊው አክለውም 529 ሺህ 570 ሄክታር መሬት 1ኛ እና 2ኛ ዙር እርሻ ሙሉ በሙሉ የታረሰ ሲኾን ከ70 በመቶ በላይ ሦስተኛ እርሻ የታረሰ መኾኑን ተናግረዋል፡፡

አቶ ንጉሴ እንዳሉት ምርታማነትን ለማሳደግ የእርሻ ድግግሞሽ፣ የግብዓት አቅርቦት እና ስርጭት፣ በመስመር መዝራት እና የኩታ ገጠም እርሻ ዋና ዋናዎቹ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡ በዞኑ በርካታ ወረዳዎች የኩታገጠም እርሻ አላቸው ያሉት ኀላፊው ወረዳዎች እንደሚያመርቱት የሰብል ዓይነት የበቆሎ፣ የጤፍ፣ የስንዴ፣ የአኩሪ አተር እና የማሽላ ተብለው እንደሚታወቁም ገልጸዋል፡፡

አርሶ አደሮች ምርታማነትን ለማሳደግ ምርጥ ዘር እና ማዳበሪያ ቀድመው በመውሰድ፣ ማሳቸውን ደጋግመው በማረስ፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት ቁርጠኝነታቸውን እያሳዩ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ አቶ ንጉሴ ለምርታማነት መጨመር ከአርሶ አደሮች በተጨማሪ የቀበሌ እና የወረዳ የግብርና ባለሙያዎች ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ አርሶ አደሮችም ማሳቸውን በወቅቱ በዘር በመሸፈን ግብዓት በአግባቡ በመጠቀም ምርታቸውን ሊያሳድጉ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳስቀመጠው ከ5 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በማልማት ከ169 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት ታቅዷል፡፡ በአማራ ክልል ለምርት ዘመኑ 8 ሚሊዮን 057 ሺህ 900 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ታቅዶ ግዥ ተፈጽሟል።
ከተገዛው ውስጥ ከ5 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ወደብ የደረሰ ሲኾን ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ደግሞ ወደ ክልሉ ገብቷል።

3 ሚሊዮን 936 ሺህ 397 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ከዩኒየኖች ወደ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ተጓጉዟል። እስካሁን ባለው አፈጻጸም 3 ሚሊዮን 547 ሺህ 340 ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች ማሰራጨት መቻሉን ቢሮው ገልጿል፡፡ ምርታማነትን በሄክታር ወደ 32 ነጥብ 7 ኩንታል ለማድረስ መታቀዱን ገልጿል፡፡

ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በኩታ ገጠም እርሻ በማልማት ከ99 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት መታቀዱንም ቢሮው ገልጿል፡፡ 897 ሺህ 809 ሄክታር መሬት በትራክተር ለማረስ 2 ሺህ 054 ትራክተሮች ጥቅም ላይ ይውላሉ ተብሎ ይጠበቃል ፡፡ 2 ሚሊዮን 462 ሺህ 422 ሄክታር መሬት በመስመር እንደሚዘራ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየተፈጠሩ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ስብራቶችን ለመጠገን ሁሉም ሊረባረብ እንደሚገባ ተገለጸ።
Next articleየሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ሰነድ የትግበራ ምዕራፍ የፍኖተ ካርታ ዝግጅት ሥራ እየተሠራ መኾኑን ፍትሕ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡