
እንጅባራ: ግንቦት 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር በቀጣይ 100 ቀናት በሚከናወኑ የልማት፣ የሰላም እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች መሪ እቅድ ላይ ያተኮረ ውይይት በእንጅባራ ከተማ ተካሂዷል። በውይይት መድረኩ የተገኙት የብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው ባለፉት ወራት በክልሉ ብሎም በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የተፈጠረው የሰላም መደፍረስ በርካታ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያ እንቅስቃሴዎችን ማስተጓጎሉን ተናግረዋል። በሰላም መደፍረስ ምክንያት የተፈጠሩ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ስብራቶችን ለመጠገን የሁሉን ርብርብ እንደሚሻም ነው ዋና አስተዳዳሪው ያነሱት።
በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በቀጣይ 100 ቀናት በተቀናጀ እንቅስቃሴ የአካባቢውን ሰላም ማረጋገጥ፣ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው መመለስ፣ የመኽር ሰብል ልማት ሥራን ማሳለጥ እና ወጣቶችን የሥራ እድል ተጠቃሚ ማድረግ ትኩረት የሚሰጥባቸው ጉዳዮች መኾናቸውን ገልጸዋል። መሪዎች የኅብረተሰቡን ተሳትፎ በማጠናከር ለእቅዶቹ መሳካት መረባረብ እንደሚገባም ዋና አሥተዳዳሪው አስገንዝበዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ ዘለቀ ከፋለ መሪ እቅዱ ባለፉት ወራት በክልሉ በተፈጠረው የፀጥታ መደፍረስ ምክንያት ተደራሽ ያልሆኑ እና የሰላም መደፍረሱን ተከትለው የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል መኾኑን ተናግረዋል።
በክልሉ የተፈጠረው የሰላም መደፍረስ በኅብረተሰቡ ዘንድ የፈጠረውን ብዥታ በማጥራት ሕዝቡን የሰላም ባለቤት የማድረግ ሰፊ ሥራ እየተከናወነ እንደኾነም ኀላፊው አንስተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም የታቀዱ እቅዶች መሬት ላይ ወርደው የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት እንዲያረጋግጡ በትኩረት እንደሚሠሩ ገልጸዋል። በውይይት መድረኩ ከሁሉም ወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳደሮች የተውጣጡ አመራሮች ተሳትፈዋል።
ዘጋቢ: ሳሙኤል አማረ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!