
ባሕር ዳር: ግንቦት20/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በምሥራቅ ጎጃም ዞን በ2016 ዓ.ም ሁለተኛዉ ዙር የሀገር መከላከያ ሠራዊት ምልመላ እየተካሄደ ነው። ሀገራቸዉን በውትድርና ለማገልገል የፈለጉ የዞኑ ወጣቶችም ወደ ማሠልጠኛ ተቋማት እየተሸኙ ነዉ። ወጣት መለሰ አሸናፊ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላትን ከተቀላቀሉት ወጣቶች ውስጥ አንዱ ነው። አባቱ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን በውትድርና እያገለገለ መኾኑን ገልጿል።
አባቱ ለሀገር እና ለሕዝብ እያገለገለ ስለመኾኑ የገለጸው ወጣት መለሰ እሱም በዛሬው ዕለት የአጎቱን እና የአክስቱን ልጆች ጨምሮ መመዝገቡን ገልጿል። “መከላከያን የተቀላቀልሁት የአባቶቻችንን አደራ ተቀብዬ ሀገሬን ለመጠበቅ ነው” ሲልም ተናግሯል ወጣቱ። የዛሬዎቹ ምልምሎች የነገ ጀኔራሎች እንኾናለን ያሉት ወጣቶቹ መከላከያን በሙያቸዉና በውትድርና ለማገልገል መነሳሳታቸውን ገልጸዋል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ አበባዉ በለጠ “የዞኑ ወጣቶች ሀገራቸውን ለመጠበቅ እያሳዩ ያሉት ሞራልና ስሜት የሚደነቅ ነው” ብለዋል። በ2016 በጀት ዓመት ሁለተኛዉ ዙር የሀገር መከላከያ ሠራዊት ምልመላ በዞኑ ከሚገኙ 18 ወረዳዎችና ከተማ አሥተዳደሮች ወጣቶች በሙያቸዉና በውትድርና ለማገልገል የሀገር መከላከያን እየተቀላቀሉ እንደኾነም ጠቁመዋል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ መረጃ እንደሚያመለክተው ሠራዊቱን በሰዉ ኃይል ለማጠናከር የመመልመል እንዲሁም ወጣቱን የክብር ሙያ ባለቤት የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም መምሪያ ኀላፊው ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!