
ባሕር ዳር: ግንቦት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጤና ቢሮ “ጽዱ ኢትዮጵያ፣ ጽዱ የጤና ተቋም” በሚል መሪ መልዕክት ጽዱ አካባቢና ጽዱ የጤና ተቋማት የመፍጠሪያ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በባሕር ዳር ከተማ ፈለገ-ህይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አካሄዷል።
በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ መሪዎች፣ የሚመለከታቸው ባለሙያዎች እና አጋር አካላት ተገኝተዋል። በመርሐ ግብሩ የተገኙት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ “ጽዱ አካባቢ እና ጽዱ የጤና ተቋማት ለመፍጠር የተጀመረውን ተግባር መሪው እና ባለሙያው በውል ተገንዝቦ ማኅበረሰቡን በማሳተፍ ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቃል” ብለዋል።
“በርካታ ለውጦች የተመዘገቡበት የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም በተለያዩ ምክንያቶች ተፋዟል” ያሉት ርእሰ መሥተዳደሩ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍና ወደ ሥራ በማስገባት የማኅበረሰቡ ጤና እንዲጠበቅ መትጋት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ በየደረጃው የሚገኙ መሪዎች ተግባሩን በቁርጠኝነት መተግበር፣ መግባባት እና ቅንጅታዊ አሠራር በማጎልበት ጽዱ አካባቢ እና ጽዱ የጤና ተቋም ለመፍጠር ትኩረት ሰጥተው እንዲመሩም አሳስበዋል። ለዕቅዱ ስኬታማነት ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲያበረክቱም ጥሪ አቅርበዋል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ ብዱልከሪም መንግሥቱ በክልሉ የእናቶችን እና ሕጻናት ጤና እንዲጠበቅ፣ ተላላፊ በሽታዎችን በመከላከል እና በመቆጣጠር ረገድ በተሠሩ ሥራዎች አበረታች ለውጦች መጥተዋል ብለዋል። ጽዱ አካባቢ እና ጽዱ ጤና ተቋም ለመፍጠር አርዓያ በመኾን በመተግበር የተሟላ የጤና አገልግሎት ለማኅበረሰቡ ማድረስ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳለው ጽዱ ጤና ተቋም መፍጠር ለሕሙማን፣ ለአስታማሚዎች እና ለባለሙያዎች ፈውስ እና እርካታ ያጎናጽፋል ያሉት ኀላፊው አካባቢን እና ተቋማትን ጽዱ ለማድረግ ሁሉም አካል ርብርብ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። የፈለገ ህይዎት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሥራ አሥኪያጅ ዐቢይ ፍስሀ የማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ በሆስፒታሉ መደረጉ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል፡፡ ሆስፒታሉ ለሕሙማን፣ ለተገልጋዮች እና ለሠራተኞች ጽዱ፣ ሳቢ እና ማራኪ እንዲኾን ሥራዎች እየተሠሩ እንደኾነ ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!