የከንቲባ ችሎት ከ20 ዓመት በላይ ሥር የሰደዱ ችግሮችን በአጭር ጊዜ በመፍታት ሁነኛ የችግር መፍቻ መንገድ ኾኖ ተገኝቷል” የደሴ ከተማ አሥተዳደር

29

ባሕር ዳር: ግንቦት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት እና የማኅበረሰቡን እርካታ በቀጥታ ለማወቅ የከንቲባ ችሎት ሁነኛ መፍትሔ ተደርጎ በከተሞች እየተሠራበት ይገኛል። አሠራሩ ተገልጋዮች፣ ከንቲባው እና የተቋማት ኀላፊዎች በተገኙበት ፊት ለፊት ጉዳያቸውን የሚያቀርቡበት መንገድ ነው። የደሴ ከተማ አሥተዳደር ደግሞ ችሎቱን ቀድሞ በመጀመር ውጤታማ ሥራዎችን እያከናወነ ነው።

የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ እንዳሉት የአገልግሎት ሰጭ ተቋማትን የእለት ከእለት የሥራ እንቅስቃሴ ግልጸኝነት እና የተገልጋዮችን እርካታ ለማወቅ ማክሰኞ እና ሐሙስ የከንቲባ ችሎት እየተካሄደ ይገኛል። በከተማ አሥተዳደሩ የከንቲባ ችሎት ከተጀመረ ከሁለት ዓመታት በላይ ማስቆጠሩን ያነሱት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ችሎቱ ከተጀመረ ጀምሮ 2 ሺህ 858 ጉዳዮችን መፍታት ተችሏል ብለዋል።

ከዚህ ውስጥ ደግሞ ከ70 በመቶ በላይ የሚኾኑት ጉዳዮች ከአምስት ዓመት በላይ የቆዩ ስለመኾናቸው ነው ያስገነዘቡት። የአንዲት የሰማንያ ዓመት አዛውንትን ጉዳይ በማሳያነት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አንስተዋል። እንደ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ማብራሪያ ግለሰቧ በከተማ አሥተዳደሩ የሚገኝ መሬታቸውን በጋራ ለመጠቀም ከቅርብ ቤተሰባቸው ጋር ይስማማሉ። አቅመ ደካማነታቸውን ያየው ግለሰብ መሬቱን ሐሰተኛ ደብተር በማሠራት በራሱ ሥም ያደርገዋል። አካባቢውም ለልማት ሲፈለግ ካሳ ተቀብሎበታል፤ በልማት ተነሽነት ሥም ደግሞ መሬት ተቀብሎ መገኘቱን ነው የነገሩን።

ለ10 ዓመታት መፍትሔ ያጡት የመሬት ባለይዞታዋ አዛውንት ከንቲባ ችሎት ሲጀመር ጉዳዩን ያቀርባሉ። ችሎቱ ጉዳዩን ሲያጣራ የአዛውንቷ ኾኖ በመገኘቱ መሬታቸውን እና ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም እንዲያገኙ መደረጉን አንስተዋል። በሌላ በኩል “መንግሥት በቀጣይ ካሳ ይከፍላቹሃል” በሚል በደብዳቤ እንዲለቁ የተደረጉ የልማት ተነሽዎችም ከ10 ዓመት በኋላ ችግሩ መፈታቱንም ነግረውናል። የከንቲባ ችሎት እስከ 20 ዓመት ሳይፈቱ የቆዩ ችግሮችን ጭምር መፍታት መቻሉን ነው ያነሱት።

የከንቲባ ችሎት በተለይም ደግሞ ሥር የሰደዱ ችግሮችን በአጭር ጊዜ በመፍታት ሁነኛ የችግር መፍቻ መንገድ ኾኖ መገኘቱን ገልጸዋል። ከከንቲባው ሳይደርሱ ታችኛው አካል ላይ ታፍነው የነበሩ አቤቱታዎችን መቅረፍ ተችሏል። ይፈጸሙ የነበሩ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን እና ሕገወጥነትን ማስተካከል መቻሉንም ገልጸዋል። ችግር ፈጥረው በከንቲባ ችሎት የተጋለጡ ግለሰቦች ላይም ሕጋዊ እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ከተሞች እና መሠረተ ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ሱለይማን እሸቱ እንዳሉት በከንቲባ ችሎት ዘርፈ ብዙ ችግሮች እየተፈቱ ይገኛሉ። አሠራሩ በአጭር ጊዜ በዝቅተኛ ወጭ ለዓመታት ሳይፈቱ የቆዩ ችግሮችን ጭምር መፍታት ያስቻለ መኾኑንም ገልጸዋል። በተለይም ደግሞ ከንቲባውን ማግኘት የተሳናቸው የተገልጋዮችን ችግር መቅረፍ ያስቻለ ነው። በደላላ ይደረግ የነበረውን አገልግሎት ጭምር መፍታት የተቻለበት መድረክ መኾኑን ገልጸዋል፡፡

የሚሰጡ ውሳኔዎችም የመደበኛውን ፍርድ ቤትን በማይጻረር መንገድ እየተከናወነ ይገኛል ነው ያሉት። በከንቲባ ችሎት የተገኙ ችግሮች በሕግ አግባብ የሚያስጠይቅ ኾኖ ከተገኘ በመደበኛው ፍርድ ቤት በጸረ ሙስና እንዲታዩ እንደሚደረግ ገልጸዋል። በከተሞች የከንቲባ ችሎት ከጀመረ ጀምሮ ወደ ቢሮው የሚመጣው የደንበኛ ቁጥር መቀነሱን ገልጸዋል። ቢሮውም በቀጣይ በተጠናከረ መንገድ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል። አሁን ላይ በክልሉ በሚገኙ ስምንት ከተሞች አገልግሎት እየተሰጠ መኾኑን ያነሱት ምክትል ኀላፊው በቀጣይ እንደ ከሚሴ፣ እንጅባራ፣ ገንዳውኃ፣ ደባርቅ እና በመሳሰሉ ከተሞችም አሠራሩን ለመተግበር ፍላጎቱ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleመንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ ታጣቂዎች ወደ ማኅበረሰቡ ተቀላቀሉ።
Next article“ጽዱ አካባቢ እና ጽዱ የጤና ተቋማት ለመፍጠር ማኅበረሰቡን በማሳተፍ ተግባራዊ ማድረግ ይገባል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ