በመርሳ ከተማ ውስጥ የሕዝቡን የመልማት ጥያቄ ለመመለስ ተስፋ ሰጭ የልማት ተግባራት እየተከናወኑ መኾኑ ተገለጸ።

14

ባሕር ዳር: ግንቦት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል እና የሰሜን ወሎ ዞን መሪዎች በመርሳ ከተማ እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል፡፡ የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) በሰሜን ወሎ ዞን መርሳ ከተማ ውስጥ የሕዝቡን የመልማት ጥያቄ ለመመለስ ተስፋ ሰጭ የልማት ተግባራት እየተከናወኑ መኾኑን ገልጸዋል፡፡

በዞኑ በሚገኙ ሁሉም ከተሞች የተጎበኙ የልማት ሥራዎች የሕዝቡን የመልማት ጥያቄ የመለሱ ተግባራት መኾናቸውንም ቢሮ ኀላፊው ተናግረዋል። ተግባራቱ ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም አሳስበዋል። የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አራጌ ይመር በበኩላቸው ይህ ልማት የመጣው ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ካለው ፍላጎት በመኾኑ ከእርስ በርስ ግጭት ወጥተን ዞናችንን እና እራሳችንን ማሳደግ ይገባናል ብለዋል።

የመርሳ ከተማ አሥተዳደር በዘንድሮ የገቢ አሰባሰብ ተግባር እስካሁን ከእቅድ በላይ የፈጸመ ሲኾን አፈጻጸሙ 103 በመቶ መድረሱን አቶ አራጌ ገልጸዋል። የመርሳ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ መሐመድ ያሲን በ2016 በጀት ዓመት ከዓለም ባንክ እና የከተማውን ኅብረተሰብ በማሳተፍ 86 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በጀት በመመደብ 21 ፕሮጀክቶች ለመሥራት መታቀዱን ገልጸዋል፡፡ እስካሁን 90 በመቶ የሚኾኑት ግንባታቸው ተጠናቅቆ ለማኅበረሰቡ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ተናግረዋል።

ግንባታቸው እየተከናወኑ ላሉ ፕሮጀክቶች የከተማው ማኅበረሰብ 13 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል፡፡ አቶ መሐመድ በቀሪ ጊዚያት ሁሉንም ፕሮጀክቶች ለማጠናቀቅ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። የልማቱ ተጠቃሚ የኾኑ የከተማው ነዋሪዎችም በሰጡት አስተያየት ረጅም ጊዜ ምላሽ ያላገኙ የሕዝቡ ጥያቄዎች በመመለሳቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል።

የሰሜን ወሎ ዞን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ መረጃ እንደሚያሳየው በመርሳ ከተማ አሥተዳደር ከተሠሩ ፕሮጀክቶች መካከል መንገድ ከፈታ፣ የውኃ ቦይ ግንባታ፣ ሸድ ግንባታ፣ የአረንጓዴ ልማት እና የቢሮ ጥገናዎች ይገኙበታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“መሪዎች በክልሉ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሚጠበቅባቸውን ኀላፊነት ሊወጡ ይገባል” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን
Next articleመንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ ታጣቂዎች ወደ ማኅበረሰቡ ተቀላቀሉ።