“መሪዎች በክልሉ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሚጠበቅባቸውን ኀላፊነት ሊወጡ ይገባል” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን

40

ደሴ: ግንቦት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የደቡብ ወሎ ዞን፣ የደሴ እና ኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር፣ እንዲሁም የወረዳዎች ጠቅላላ መሪዎች በተገኙበት በወቅታዊ የሰላም፣ ልማት እና መልካም አሥተዳደር ላይ ትኩረቱን ያደረገ የምክክር መድረክ በደሴ ከተማ ተካሂዷል፡፡ በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር) ወቅታዊ የፓለቲካ፣ የሰላም፣ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች ዙሪያ የውይይት መነሻ ሰነድ አቅርበዋል።

ባቀረቡት ሰነድም በአማራ ክልል በሚቀጥሉት 100 ቀናት የሚተገበሩ ቁልፍ ዕቅዶች ተለይተው ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ስለመገባቱ አስገንዝበዋል፡፡ የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን ሕዝቡ፣ አመራሮች እና የጸጥታ ኀይሉ ተቀናጅቶ በመሥራቱ ዞኑ በተረጋጋ ሰላም ውስጥ ይገኛል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ “የገጠመውን የጸጥታ ችግር ተቋቁሞ በማለፍ የማጥራት ምዕራፍ ላይ እንገኛለን” ብለዋል፡፡ የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ መሐመድአሚን የሱፍ የክልሉ ሕዝብ ጥያቄዎች የሚፈቱት በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እና በተረጋጋ መንገድ እንጂ ያለውን ሃብት እና እሴት በማጥፋት መኾን እንደሌለበት መግባባት መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡ ከኅብረተሰቡ ጋር በተፈጠረው መግባባት በከተማ አሥተዳደሩ በሁሉም ዘርፍ በርካታ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ስለመኾኑም አስረድተዋል፡፡

የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን “መሪዎች ራሳቸውን ከችግሩ በመነጠል፣ የሚያጋጥሙትን ችግሮች ሰንጥቆ በማለፍ እና እምነትን በመገንባት በክልሉ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሚጠበቅባቸውን ኀላፊነት ሊወጡ ይገባል” ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡ “መሪዎች በክልሉ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሚጠበቅባቸውን ኀላፊነት ሊወጡ ይገባል” ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ፡- አንተነህ ፀጋዬ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየተጠባባቂ ጥሪ ማስታወቂያ !
Next articleበመርሳ ከተማ ውስጥ የሕዝቡን የመልማት ጥያቄ ለመመለስ ተስፋ ሰጭ የልማት ተግባራት እየተከናወኑ መኾኑ ተገለጸ።