“ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የግንኙነት መድረክ ያላት ተቀባይነት ማደጉ የብሪክስ አባል መኾኗ ለሚያስገኝላት ጥቅም ማሳያ ነው” አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን

17

ባሕር ዳር: ግንቦት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ የብሪክስ ጥምረትን መቀላቀሏ በዓለም አቀፍ ተቋማት ምስረታ እና በአባልነት ያላት ታሪካዊ ሚና እያደገ መምጣቱ ማሳያ እንደኾነ በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ የመንግሥታቱ ማኅበር፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የአፍሪካ ኅብረት እና ሌሎች ድርጅቶች እንዲመሰረቱ ጉልህ ሚና ካላቸው ሀገራት አንዷ እንደኾነችም ነው የተናገሩት።

አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን “ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የግንኙነት መድረክ ያላት ተቀባይነት ማደጉ የብሪክስ አባል መኾኗ ለሚያስገኝላት ጥቅም ማሳያ ነው” ሲሉም ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ካላት ሊለማ የሚችል እምቅ የተፈጥሮ ጸጋ፣ እና ሰፊ አምራች የሰው ኃይል አኳያ እያደገ በመጣው የደቡብ – ደቡብ ትብብር ገንቢ ሚና መጫወት እንደምትችል ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ እና ሩሲያ በሕዝብ ለሕዝብ እና በልማት የትብብር መስኮች ታሪካዊ እና በመተማመን ላይ የተመሰረተ ወዳጅነት እንዳላቸው አንስተዋል። የብሪክስ ጥምረትም የሀገራቱን የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን አጋርነት ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር የጋራ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማስቀጠል እንደሚረዳ አብራርተዋል።

የብሪክስ አባል ሀገራትም በዕድገት እና ሥልጣኔ፣ በባሕል እና ቀጣናዊ የልማት ትብብር መስክ ገንቢ የምክክር እና ውይይት ባሕል እያዳበሩ መኾናቸውን አስረድተዋል። ብሪክስ ከዓለም ጥቅል ዕድገት 35 ነጥብ 6 በመቶ በመሸፈን የተሻለ የኢኮኖሚ ልማት አቅም ያለበት ጥምረት መኾኑንም አመላክተዋል።

ኢዜአ እንደዘገበው የጥምረቱ አባል ሀገራትም በዓለም ኢኮኖሚ ውስጥ 58 ነጥብ 9 ትርሊዮን የአሜሪካን ዶላር ድርሻ እና በሕዝብ ብዛትም 45 ከመቶውን በመያዝ ከፍተኛ አቅም እንዳላቸው ገልጸዋል። በብራዚል፣ ሩሲያ፣ ህንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ የተመሰረተው ብሪክስ በነሐሴ/2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ጆሀንስበርግ ከተማ ባካሄደው 15ኛው የመሪዎች ጉባኤ ኢትዮጵያ፣ ግብጽ፣ የተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች፣ ሳዑዲ አረቢያ እና ኢራን የጥምረቱ አባል እንዲኾኑ መወሰኑ ይታወቃል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ምክክር ሊያካሂድ መኾኑ ተገለጸ።
Next articleየተለያዩ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለኅብረተሰቡ በማቅረብ የገበያ መረጋጋት ሥራ እየተሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ገለጸ።