
አዲስ አበባ: ግንቦት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከግንቦት 21 እስከ ግንቦት 27/2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ውስጥ የሚያካሂደውን የምክክር ምዕራፍ በተመለከተ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል። መግለጫውን የሰጡት ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረስላሴ የምክክር ጉባኤው ከ2 ሺህ 500 በላይ ተወካዮችን እንደሚያሳትፍ ገልጸዋል።
የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የሚወክሉ ተሳታፊዎች፣ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ባለድርሻ አካላት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የሲቪክ ማኅበራት እና የመንግሥት አካላት፣ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የተለያዩ ተቋማት እና ማኅበራት ተወካዮች የሚመካከሩበት እና በሀገራዊ ጉባኤው የሚወክሏቸውን ተሳታፊዎች የሚመርጡበት እንደኾነም አንስተዋል።
ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት በዚህ የምክክር መድረክ ሦስት ዋና ዋና ተግባራት ይከናወኑበታል ብለዋል፡፡ በመጀመሪያ የሚመጡ ተሳታፊዎች በምክክር እና በውይይት የአጀንዳ ሀሳቦችን ያመጣሉ፤ ቀጥለው አጀንዳዎቻቸውን የጋራ በማድረግ ያሰባስባሉ፣ ያደራጃሉ፣ የመፍትሔ ሃሳቦችን ያንሸራሽራሉ፤ በመጨረሻም የሂደቱ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ተሳታፊ የሚኾኑ ተወካዮቻቸውን ይመርጣሉ ሲሉ በመግለጫው አብራርተዋል።
ዘጋቢ፡- ቤቴል መኮንን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!