“ወጣቶችን ከአደንዛዥ እና አሉታዊ መጤ ልማዶች ለመጠበቅ ንቅናቄዎችን በማዘጋጀት እየሠራን ነው” ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ.ር)

21

አዲስ አበባ: ግንቦት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ወጣቶችን ከአደንዛዥ እና አሉታዊ መጤ ልማዶች ለመጠበቅ ንቅናቄዎችን በማዘጋጀት እየሠሩ መኾኑን ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ.ር) ገልጸዋል፡፡ የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የፀረ-አደንዛዥ እፆች እና አሉታዊ መጤ ልማዶች በታዳጊዎች እና በወጣቶች ሰብዕና ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ በመከላከል ሰብዕናቸውን ለመገንባት የሚረዳ “ከሚያዚያ እስከ ሚያዚያ” በሚል የተዘጋጀው ንቅናቄ የደረሰበት ደረጃ እና በቀጣይ የሚሠራባቸው እቅዶች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።

በውይይቱ ላይም ከፌዴራል መስሪያ ቤቶች፣ ከክልሎች እና ከከተማ አሥተዳደሮች የተወጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል። በውይይቱ ላይም በንቅናቄ የተሠሩ ሥራዎች እና ያጋጠሙ ችግሮች ለተሳታፊዎች ቀርበዋል። በውይይቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ.ር) “ወጣቶች ለሀገር ትልቅ ሃብት ናቸው” ብለዋል፡፡ በመኾኑም ወጣቶችን ከአደንዛዥ እና ከአሉታዊ መጤ ልማዶች ለመጠበቅ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተለያዩ ንቅናቄዎችን በማዘጋጀት በሥራ ላይ ነው ብለዋል።

የፀረ አደንዛዥ እና መጤ ልማዶች የሀገር ሃብት የኾኑ ወጣቶችን በከፍተኛ ሁኔታ በመጉዳት ላይ ናቸው ብለዋል፡፡ ዶክተር ኤርጎጌ እነዚህ ወጣቶችን ለመታደግ እና የሱስ ተጠቂ የኾኑትንም ለማዳን ሁሉም ባለድርሻ አካላት ትብብር ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል። ከሚያዚያ እስከ ሚያዚያ በሚለው ንቅናቄ በተሠሩ ሥራዎች ላይም ከ12 ሺህ በላይ የሺሻ መጠቀሚያ እቃዎችን፣ 70 ኪሎ ግራም አደንዛዥ እፆች መወገዳቸው፣ 738 የሺሻ ንግድ ቤቶች እና በሕገ ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የስፖርት ውርርድ ቤቶች ላይ እርምጃ እንደተወሰደባቸው በቀረበው ሪፖርት ላይ ተጠቅሷል።

ዘጋቢ፡- ራሔል ደምሰው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የአማራ ሕዝብ መብት እና ጥቅም ማስከበር የጋራ አጀንዳችን ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next articleየኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ምክክር ሊያካሂድ መኾኑ ተገለጸ።