“የአማራ ሕዝብ መብት እና ጥቅም ማስከበር የጋራ አጀንዳችን ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

69

ባሕር ዳር: ግንቦት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በአማራ ክልል ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጋር እየተወያዩ ነው። በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲ የጋራ ምክር ቤት ሰብሣቢ ተስፋሁን ዓለምነህ አዲስ የፖለቲካ ምህዳር እንዲሰፋ የፖለቲካ ፓርቲዎች መቃወም ላይ መሠረት ካደረገ እንቅስቃሴ በመላቀቅ በተፎካካሪነት ውስጥ በትብብር ለሀገር መሥራት እንዲችሉ ታሳቢ ተደርጎ የጋራ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤት መመሥረቱን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ መተማመን እና ሰላምን መሠረት ያደረገ ግንኙነት እንዲኖር የጋራ ምክር ቤቱ መመሥረቱን ገልጸዋል። ችግሮችን በጋራ ለመፍታት መተማመን እና ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዲኖር የጋራ ምክር ቤቱ ማስፈለጉን አንስተዋል። በተለያየ የፖለቲካ አቋም ውስጥ ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ ውይይት ለመፍጠር ወሳኝ መኾኑንም አመላክተዋል። በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የእርስ በእርስ ግጭት ትልቅ ቦታ ያለው በመኾኑና ችግሩን ለመፍታት የሠለጠነ ሰላማዊ የፖለቲካ ትብብር አስፈላጊ በመኾኑ የጋራ ምክር ቤት ማቋቋም ማስፈለጉን ገልጸዋል። የጋራ ሀገር እና የጋራ ሕዝብ እስካለ ድረስ በትብብር መሥራት ይጠበቃል ነው ያሉት።

የጋራ ምክር ቤቱ ምርጫ በሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ በኾነ መንገድ እንዲጠናቀቅ፣ በተለያየ ጊዜ የሃሳብ ልዩነቶች ወደ ግጭት እንዳያመሩ ምክረ ሃሳቦችን በማቅረብ፣ በሕልውና ጦርነቱ ጊዜ የጋራ ምክር ቤቱ በጋራ በመወሰን የማይተካ ሚና ተጫውቷል ነው ያሉት። በኅብረተሰቡ ውስጥ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱም ገልጸዋል። ለሰላም ግንባታ እና መረጋጋት ውይይት እና ድርድርን ማስፋት ይገባል ብለዋል። አለመግባባቶችን ለመፍታት ሰላማዊ ውይይቶችን ማድረግ ይገባልም ብለዋል።

የፖለቲካ ጥያቄ አለኝ የሚል አካል ውይይትን መቀበል አለበት ነው ያሉት። የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሀገር ማሰብ እና ለሀገር መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም አንስተዋል። መንግሥት ብቻ ሳይኾን በፖለቲካ ፓርቲዎችም ተጠያቂነት አለ ነው ያሉት። የፖለቲካ ፓርቲዎች መቻቻል እና ብዝኃነትን ማሳደግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ብዝኃነትን እና መቻቻል አስፈላጊ ጉዳይ ነው ያሉት ሠብሣቢው መቻቻል እና ብዝኃነት ላይ መሥራት ካልተቻለ ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ አይቻልም ነው ያሉት። የፖለቲካ ፓርቲዎች ለማኅበራዊ ፍትሕ መሟገት እንደሚገባቸውም ተናግረዋል። ፖለቲካ አቅም፣ አቋም እና ተሻጋሪነትን ይጠይቃልም ብለዋል።

ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ የሚመክሩበት አውድ በኢትዮጵያ ብዙ የተለመደ እንዳልነበር አንስተዋል። ችግሮችን በውይይት ከመፍታት ይልቅ ሌሎች አማራጮችን የመጠቀም ልምድ እንደነበርም ገልጸዋል። አሁን የተፈጠረው አውድ እና ችግሮችን በጋራ ለመፍታት የሚደረጉ ውይይቶች የሚደነቁ መኾናቸውን ተናግረዋል።

“የአማራን ሕዝብ መብት እና ጥቅም ማስከበር የጋራ አጀንዳችን ነው” ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የአማራ ክልልን ሉዓላዊነት ማስከበር ሌላው የጋራ አጀንዳ መኾኑንም ገልጸዋል። አብረን ለመሥራት የሚያስገድዱን ጉዳዮች አሉም ብለዋል። በጋራ የሚደረጉ ውይይቶች ወሳኝ መኾናቸውንም አንስተዋል።
የፓርቲ ለፓርቲ፣ የፓርቲ እና የመንግሥት፣ የፓርቲ እና የሕዝብ ውይይቶች እንደሚያስፈልጉም ገልጸዋል። “በጋራ ሥንሠራ የክልሉን መብት እና ጥቅም እናስከብራለን፣ ከአደጋ እንጠብቀዋለን” ነው ያሉት። ሃቅ ላይ የተመሠረተ ውይይት እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleወጣቶችን አብቅቶ ወደ ሥራ ማሰማራት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ አስታወቀ።
Next article“ወጣቶችን ከአደንዛዥ እና አሉታዊ መጤ ልማዶች ለመጠበቅ ንቅናቄዎችን በማዘጋጀት እየሠራን ነው” ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ.ር)