ወጣቶችን አብቅቶ ወደ ሥራ ማሰማራት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ አስታወቀ።

34

ባሕር ዳር: ግንቦት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የሙያ እና ቴክኒክ ኮሌጆች ወጣቶችን በዕውቀት፣ በክህሎት እና በአመለካከት አንጸው ሥራ ፈጣሪ በማድረግ ብቁ ዜጋ የማፍራት ኀላፊነት አለባቸው ተብሏል። ባሕር ዳር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅም ወጣቶችን እየተቀበለ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች እያሠለጠነ ይገኛል። ከማሠልጠን በተጨማሪም የስብዕና ግንባታ እና የሥራ ዕድል ፈጠራ አማራጮችን በመጠቀም ወደ ሥራ እንዲሰማሩ እያደረገ ነው።

ሰላማዊት አቦ ከባሕር ዳር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ በደረጃ አምስት ሠልጥና ተመርቃለች። በሥልጠና ቆይታዋ ከቀለም ትምህርት በተጨማሪ በሥራ ፈጠራ፣ በደንበኛ አያያዝ፣ በአመራርነት እና በካይዘን ጭምር መሠልጠኗን ገልጻለች። በዚህም ዕድለኛነቷን ትናገራለች። ”ቴክኒካዊ ክህሎቱ ዘርፉን ስለመረጥኩት ብማረውም የበለጠ ብቁ ያደረገኝ ደግሞ የተግባቦት እና የሶፍት ስኪል መሠልጠኔ ነው” ትላለች።

ሰላማዊት ኮሌጁ ባዘጋጀው አውደ ርዕይ ዕውቀት፣ ክህሎት፣ አመለካከት እና የሥራ ተነሳሽነቷን አስተዋውቃ ካፒታል የገንዘብ ቁጠባ እና ብድር አክሲዮን ማኅበር በተባለ ድርጅት ተቀጥራለች። በኤሌክትሪካል እቃዎች መካኒካል ምህንድስና በደረጃ አራት ተምሮ የብቃት ፈተናን ያለፈው ክንዴነህ ደርሶም ኮሌጁ ከዕውቀት እና ክህሎት በተጨማሪ በሥነ ልቦና አሠልጥኖ ለሥራ ብቁ እንዳደረገው ነው የሚገልጸው። ሠልጣኞች በየተቋማት እየተላኩ የሥራ ላይ ሥልጠና መውሰዳቸውንም አስረድቷል። የሞተር አጠቃቀም እና ደኅንነት ቁጥጥር ፕሮጀክትም ከጓደኞቹ ጋር አዘጋጅቶ አስጎብኝቷል። እሱም የሥራ ዕድል ተፈጥሮለት በሙከራ ቅጥር ላይ ይገኛል።

ሰላማዊት እና ክንዴነህ ባሕር ዳር ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ተማሪዎችን ብቁ እና ሥራ እንዲያገኙ ለማድረግ ላደረገው ጥረት አመሥግነዋል። ሌሎች የትምህርት ተቋማትም መሰል የሥራ ዕድሎችን ለተመራቂዎቻቸው እንዲያመቻቹ አሳስበዋል። በባሕር ዳር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የትምህርት እና ሥልጠና ምክትል ዲን ባንታየሁ ስንቴ ኮሌጃቸው በተግባር እጁ የተፍታታ እና ገበያው የሚፈልገውን ባለሙያ ለማፍራት በጥናት ተመስርቶ እንደሚያሠለጥን ገልጸዋል።

ሠልጣኞች በዕውቀት እና ክህሎት እንዲበቁ ታስቦ እንደሚሠራ የገለጹት ምክትል ዲኑ ሥራ እንዲፈጥሩ ወይም እንዲያገኙ ታልሞ እየተሠራ መኾኑን ነው የተናገሩት። ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር እና የማሠልጠኛ ቁሳቁሶች በማሟላት ሠልጣኞችን ብቁ ማድረግም ትኩረት መሰጠቱን ጠቅሰዋል። ኮሌጁ የሥራ አውደ ርዕይን ጨምሮ በተለያዩ አማራጮች ባለሃብቶችን በማወያየት ተመራቂዎቹ ወደ ሥራ እንዲሰማሩ እያደረገ መኾኑን ነው ምክትል ዲኑ የተናገሩት። ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስም ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር አምስት ሁነቶችን በማዘጋጀት ተመራቂዎቹን እና ቀጣሪዎችን የማገናኘት ሥራ መሠራቱን ነው የገለጹት። ጥሩ ውጤት ተገኝቷል፤ ተጠናክሮም ይቀጥላል ብለዋል።

ኮሌጁ በተናጠልም ኾነ በኢንተርፕራይዝ ተደራጅተው ሥራ የፈጠሩ ተመራቂ ወጣቶችንም ድጋፍ እያደረገ መኾኑ ነው የተገለጸው። በተያዘው በጀት ዓመት 45 መምህራንም በካይዘን፣ በቴክኖሎጂ፣ በክህሎት እና በሥራ ፈጠራ ፓኬጆች የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ድጋፍ እያደረጉ መኾኑን ምክትል ዲኑ ገልጸዋል። ጥሩ ግብረ መልስም አግኝተንበታል ብለዋል።

ወጣቶችን በዕውቀት፣ በክህሎት እና በአመለካከት አሠልጥኖ ውጤታማ ለማድረግ ብዙ ጊዜ የሚጠይቅ ቢኾንም ባለፉት ጊዜያት ሥራ የፈጠሩ እና ሠራተኛም የቀጠሩ በመኖራቸው ውጤት እያገኘንበት ነው ብለዋል። ከአፈጻጸማቸው ሌሎቹ ኮሌጆች እንዲማሩበት በመተባበር እና በመማማር እየሠሩ መኾኑንም ጠቅሰዋል።

በአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ ተወካይ ምክትል ቢሮ ኀላፊ ሙላው ልመንህ በክልሉ ሠልጣኝ ተመራቂዎች የመመረቂያ ፕሮጀክት አዘጋጅተው እያቀረቡ ወይም ቀጣሪ ድርጅቶች እና ተመራቂዎችን በአውደ ርዕይ የማገናኘት ስልት እየተተገበረ መኾኑን ገልጸዋል። ኮሌጆች ወጣቶችን አስመርቆ ከመሸኘት ይልቅ ተመራቂዎቻቸው በራሳቸው ሥራ እንዲፈጥሩ ወይም የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ማድረግ በሥራና ሥልጠና ቢሮ አሠራር የተቀመጠ ስልት መኾኑን ገልጸዋል። ገበያ ተኮር ሥልጠና መስጠትም ከኮሌጆች የሚጠበቅ መኾኑን ጠቅሰዋል።

ቡሬ፣ ደብረ ብርሃን እና ጎንደር ላይም መሰል ሥራ መጀመሩን እና ባለፉት ዓመታትም አበረታች ጅምር መታየቱን ተወካይ ኀላፊው ገልጸዋል። ኢንዱሥትሪዎችም ብቁ ባለሙያ ለማግኘት ከኮሌጆች ጋር ተባብረው ቢሠሩ መልካም ነው ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየደቡብ ወሎ ዞን፣ የደሴ እና ኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር በወቅታዊ ተግባራት ዙሪያ ምክክር እያካሄዱ ነው።
Next article“የአማራ ሕዝብ መብት እና ጥቅም ማስከበር የጋራ አጀንዳችን ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ