
[ 🌴 ልዩ ጥንቅር🌴 ]
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በውበቷ ላማረች፣ በጸጋዋ ለተወደደች፣ በተፈጥሮ ለተሞሸረች፣ ረጅሙን ወንዝ ለታጠቀች፣ በምስጢራዊ ሐይቅ ለታቀፈች፣ እንደ ንጉሥ ሰልፈኛ በሥርዓት በቆሙ ዘንባባዎች እጥፍ ድርብ ውበትን ለተጎናጸፈች፣ ባማሩ ጎዳናዎች ለተሞሸረች፣ በሚያውቃትም በማያውቃትም፣ ባዩዋትም ባላዩዋትም ለተወደደች ውብ ሥፍራ አዲስ ውበት ተሰጥቷታል።
ጀምበር በምሥራቅ ስትዘልቅ ውበቷ አብሮ የሚዘልቀው፣ ጸጋዋ ነግቶ እስኪታይ ድረስ የሚናፍቀው ይህች ውብ ሥፍራ ጀምበር ስትጠልቅ፣ ምሽቱን ከሚያደምቁት ከጨረቃና ከከዋክብት ጋር ኅብረት እየፈጠረ ውበቷን የሚያደምቅ፣ የመወደዷን ነገር አብዝቶ የሚያስናፍቅ አዲስ ውበት ተጨምሮላታል። በምሽትም በቀንም ሲያዩዋት ታሳሳለች፣ በአሻገር ያሉትን ቀልብ ትስባለች፣ በውበቷ ትጣራለች፣ በፍቅሯ ታስራለች።
ለክብሯ እጅ እየነሱ አገልጋዮቿ ለተልእኮ እንደሚፋጠኑላት፣ ከራሷ ዘውዷን እንደሚጭኑላት፣ በትክሻዋ ወርዶ እስከ እግር ጥፍሯ ድረስ ውበትን የሚሰጥ ካባ እንደሚደርቡላት፣ ለዓይን የሚያብረቀርቀውን የእጅ አምባር እንደሚያጠልቁላት፣ ያማረ መጫሚያ በእግሮቿ ላይ እንደሚያጫሟት፣ ድባብ ዘርግተው እንደሚከተሏት፣ አቧራ እንዳይነካት እየቀደሙ እንደሚከልሉላት፣ ዓይነ እርግብ ዘርግተው ለክብሯ እንደሚጨነቁላት፣ ጮማ እየቆረጡ፣ ጠጅ እያዘነበሉ እመቤት እያሉ እንደሚንከባከቧት፣ ከአጠገቧም እንደማይርቋት ንግሥት ሁሉ ሰው ሲያጅባት ውሎ ሲያጅባት ያመሻል፣ በመሸም ጊዜ ነግቶ እስኪያያት፣ ዳግም በውበቷ እስከሚደሰትባት እያሰበ ወደቤቱ ይገባል።
ለዘመናት በታጠቀችው፣ ከውበት ላይ ውበት ደርባ በኖረችው ግዮን የተሠራ አዲስ ድልድይ ለእርሷ አዲስ ውበት፣ ለነዋሪዎቿ እና ለጎብኝዎቿ አዲስ ሀሴት ኾኗል። በግዮን ላይ አምሮ የተሠራው፣ ከማዶና ማዶ ኾነው የሚኖሩትን እያሻገረ የሚያገናኘው ድልድይ ከድልድይ ባሻገር ነው። ውበት ነው ውቧ ከተማ አብዝታ የምትዋብበት፣ ጌጥ ነው አምራ የምታጌጥበት፣ መገለጫ ነው በሩቅ የምትታወቅበት፣ ቅርስ ነው ልጆቿን የምታስተምርበት፣ መስህብ ነው ጎብኝዎችን የምትጠራበት፣ ማዕድ ነው ለእንግዶቿ ፍቅርን የምታቋድስበት፣ መሶበ ወርቅ ነው ያማሩ የእጅ ሥራዎችን የምታሳይበት፣ እልፍኝ ነው የሩቅ እና የቅርቡን አገናኝታ የምትደግስበት፣ የገቢ ምንጭ ነው ውበቱን ብለው ከሚመጡ ገንዘብ የምታገኝበት በታላቁ ወንዝ የተሠራው ታላቁ ድልድይ ለባሕርዳር ከተማ ብዙ ነገሯ ነው።
ለወትሮው ጥሻ የበዛበት አካባቢ ጸድቶ እጅግ ያማረ ውበትና ግርማ ያለው ድልድይ ተገንብቶበታልና የከተማዋ ነዋሪዎች አዲስ ውበት አግኝተዋል። ወደ ከተማዋ የሚመጡ እንግዶችም ከዚህ ቀደም አይተውት የማያውቁትን ያማረ ነገር ተመልክተዋል። ጀምበር ስታዘቀዝቅ፣ በምዕራብ ልትጠልቅ ስትፋጠን የባሕርዳር ከተማ ነዋሪዎች ከተለያየ አቅጣጫ ወደ አዲስ ድልድይ ወደ ተሠራበት ወደ ግዮን ያቀናሉ። ልጆች ከእናት እና አባቶቻቸው ጋር ኾነው በደስታ ይቦርቃሉ። ፍቅረኛሞች በፍቅር በአዲሱ ድልድይ ሽርሽር ይላሉ። ጓደኛሞች የጎደኝነትን መልካም ጊዜ በግዮን በአዲሱ ድልድይ ያሳልፋሉ። ያረጁትም ሰዎች በእርጅና ዘመናቸው ያዩት አዲስ ውበት ነውና በውበቱ ለመደነቅ ወደ አዲሱ ድልድይ ያቀናሉ።
በድልድዩ ላይ የተገጠሙት ኅብረ ቀለማት ያሏቸው መብራቶች ከጨለማው ጋር ኅብረት ፈጥረው አካባቢውን በውበት ይመሉታል። በዚያ ሥፍራ ከዚያ ቀደም ያን የመሠለ ውበት ታይቶ አይታወቅም እና ብዙዎች በደስታ ይከንፋሉ፣ ምሽቱን በግዮን ላይ በአዲሱ ድልድይ ያሳልፋሉ። በድልድዩ ውበት፣ በምሽቱ መብራት ይደነቃሉ፣ አብዝተውም በሀሴት ይከንፋሉ።
የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ ስለ ድልድዩ ሲናገሩ ለከተማችን ትልቅ አርማ ኾኖ የሚያገለግል ነው፣ የከተማዋን ገጽታ በከፍተኛ ሁኔታ የሚቀይር፣ ለከተማዋ መለያ የሚኾን፣ ለሕዝብ ደስታን የፈጠረ፣ የከተማዋን ውበት አሁን ካለበት የበለጠ ከፍ የሚያድርግ፣ የቱሪዝም መዳረሻ የሚኾን፣ ከተማዋን በመላው ኢትዮጵያ እና በመላው ዓለም የሚያስተዋውቅ ነው ይሉታል።
ድልድዩ ሰሜኑን ኢትዮጵያን ከሌላው የኢትዮጵያ ክፍል የሚያገናኝ፣ አህጉር አቋራጭ ከኾነው የአፍሪካ መንገድ መካከል አንዱ በመኾኑ፣ የሕዝብን ትስስር በመፍጠር የባሕርዳርን የቱሪዝም እንቅስቃሴ በከፍተኛ ደረጃ ከፍ የሚያደርግ፣ ለቀጣናው ትኩረት የሚስብ፣ ከፍ ተደርጎ ሊታይ የሚገባው ነው ይላሉ። ድልድዩ የትውልድ ስጦታ ነውም ይሉታል።
እንደ እርሳቸው ገለጻ በድልድዩ ዙሪያ ያማሩ ሆቴሎች ይገነባሉ። በከተማዋ ታላላቅ ባለኮኮብ ሆቴሎች እየተስፋፉ ነው፣ ታላላቅ ባለሃብቶች ወደ ከተማዋ እየመጡ ነው። በአዲሱ ድልድይ ማዶ ሦስት ባለ አምስት ኮኮብ ሆቴሎች መገንቢያ ቦታዎች ተሰጥተዋል። ሁለቱ የቦታ ርክክብ ተደርጓል። አትሌት ኃይለ ገብረ ሥላሴ በከተማዋ የሆቴል ግንባታ ለመገንባት ከ30ሺህ በላይ ካሬ ሜትር ቦታ በዓባይ ማዶ አጼ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ መረከቡንም አንስተዋል። የሐይቅ እና የወንዝ ዳር ልማቶችም ይቀጥላሉ ነው ያሉት።
በድልድዩ በሁለቱም አቅጣጫ ለቱሪዝም የሚያመች ውብ ሥፍራ ነው። ትልልቅ ሆቴሎች ከትልቁ ድልድይ ጋር በውበት አብረው ለከተማዋ ውበት ይሰጣሉ። የከተማዋን ቱሪዝምም ከፍ ያደርጋሉ ይላሉ። በድልድዩ ምሥራቃዊ አቅጣጫ በተለምዶ ዓባይ ማዶ በሚባለው አካባቢ ያማሩ ሆቴሎች፣ ምዕራባዊ አቅጣጫ ደግሞ የክልሉ ቤተ መንግሥት ተውቦ ይሠራበታል። ይሄም ሌላ ውበት፣ ሌላ ገጽታ፣ ሌላ ተወዳጅነት ነው።
” ዓባይ በጣና ላይ እንዴት ቀለደበት
ለአንድ ቀን ነው ብሎ ዘላለም ሄደበት”
እየተባለ በቅኔ ሲነገር ከኖረበት፣ የዓባይ እና የጣናን አስደናቂ የተፈጥሮ መለያያ ከኾነበት፣ ውኃ በላይ እና በታች ኾነው ከሚተላለፊበት፣ ያማረውን ነገር፣ የተፈጥሮውን ድንቅ ነገር ለማየት ብዙዎች ሲጓዙበት ከኖሩበት ከዓባይ እና ከጣና መለያያ ጀምሮም አዲስ የውበት ሰገነት ለመሥራት ታስቧል ነው ያሉት። ይሄን ድንቅ የተፈጥሮ ውበት የሚያሳምር፣ ከተማዋን ለበለጠ የቱሪዝም መዳረሻ የሚያደርግ ሥራ ይሠራል ይላሉ ምክትል ከንቲባው። ሥራው ዓባይ ከጣና ተለይቶ ከሚወጣበት ጀምሮ በቀድሞው ድልድይ አልፎ እስከ አዲሱ ድልድይ ድረስ የሚደርስ ነው።
በግዮን ዳርቻ የከተማዋን ውበት የሚያጎሉ የመዝናኛ እና የንግድ ተቋማት ይገነባባቸዋል፣ ሥራውም ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ፣ ታሪክ እና እሴትን ያከበረ ነው። አሁን ባሕርዳር ከቀደመው ይልቅ ተሞሽራለች፣ የበለጠ ለማማር እና ለመሞሸር ሽርጉድ ላይ ነች። ያን ጊዜ ከውበት ላይ ውበት ደርባ፣ ከጌጥም ላይ ጌጧን ደራርባ አሸብርቃ ትታያለች።
እስካሁን በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ታይቶ የማይታወቀውን፣ በእርዝመቱ፣ በውበቱ፣ በስፋቱ እና በጥራቱ አቻ የሌለውን በታላቁ ወንዝ የተገነባውን ታላቁን ድልድይ ተመልከቱት። ደስታን ታተርፉበታላችሁ። መልካም ያሰቡ አዕምሮዎችን፣ አሳምረው የሚሠሩ እጆችን ታደንቁበታላችሁ።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!