
ባሕር ዳር: ግንቦት 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ደብረ ብርሃን ከተማ በኢንቨስትመንት ዘርፍ በእድገት ላይ ከሚገኙ ከተሞች ከቀዳሚዎቹ ተርታ ትጠቀሳለች፡፡ ለማዕከላዊ ገበያ ባላት ቅርበት እና የሰላም ከተማነቷ በባለሃብቶች ዘንድ እንድትመረጥ አድርጓታል፡፡
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተሞች ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተሞች እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አህመዲን መሐመድ (ዶ.ር) ጨምሮ ከፍተኛ የክልሉ እና የከተማ አሥተዳደሩ የሥራ ኀላፊዎች በከተማዋ ጉብኝት አድርገዋል፡፡
በከተማ አሥተዳደሩ የሚከናወኑ የሌማት ትሩፋት የልማት ሥራዎችም በጉብኝቱ ታይተዋል፡፡
በተለይ የሌማት ትሩፋት ከአረብ ሀገራት ተመላሾችን ጨምሮ ለበርካታ ወገኖች የሥራ ዕድል ለመፍጠር መሠረት ተደርጎ መተግበሩን በጉብኝቱ ወቅት ተጠቁሟል፡፡
በከተማው የሚከናወኑ የሌማት ትሩፋት ሥራዎች ተስፋ የሚጣልባቸው እና አበረታች ለውጥ የታየባቸው እንደኾነ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተሞች ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተሞች እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አህመዲን መሐመድ (ዶ.ር) ገልጸዋል።
በግልም ይሁን በኢንተርፕራይዞች ለተሰማሩ ወጣቶች አጫጭር ሥልጠናዎችን በመስጠት ድጋፍ እያደረገ ያለው የደብረ ብርሃን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅም የጉብኝቱ አካል ነበር፡፡
ኮሌጁ ለሥራ ዕድል ፈጠራ ተልእኮ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ እንዲቀጥል ዶክተር አህመዲን አሳስበው በክልሉ መንግሥት አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግለትም ተናግረዋል፡፡
ከሌማት ትሩፋት በተጓዳኝ በከተማው እየተሠሩ ያሉ የቢሮ ግንባታዎች እና የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች በሥራ ኀላፊዎቹ ተጎብኝተዋል፡፡
በኅብረተሰቡ እና በመሪዎች መካከል ጠንካራ ግንኙነት በመፍጠር የልማት ሥራዎቹ በዕቅዳቸው መሠረት መከናወናቸውን ስለመመልከታቸው ዶክተር አህመዲን ገልጸዋል።
ከተማዋ ያላትን የኢንቨስትመንት ተመራጭነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ለባለሃብቶች ቀልጣፋ፣ ፍትሐዊ እና ፈጣን አገልግሎት በመስጠት የተጀመረው የልማት ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ዶክተር አህመዲን አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ስንታየሁ ኃይሉ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!