
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የጦር ኀይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀኔራል አበባው ታደሰ የኮማንዶ እና አየር ወለድ ዕዝ ማሠልጠኛ ማዕከል አሠልጥኖ ላስመረቃቸው የበታች ሹም አመራሮች በወቅታዊ ተቋማዊ ሀገራዊና አካባቢያዊ ሁኔታዎች ላይ ገለጻ አድርገዋል።
በገለጻቸውም የኢትዮጵያን ትልቅነት የሚረዱ ታሪካዊ ጠላቶች በገንዘብ በቀጠሯቸው የውስጥ ተላላኪዎች የተለያዩ ሀገር አፍራሽ አጀንዳ በመስጠት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ትንኮሳ ለመፈጸም ቢሞክሩም በጀግናው ሠራዊት ክቡር እና ውድ መስዋዕትነት ክፉ ህልማቸው እንዳይሳካ ተደርጓል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የማይገባትን ጥቅም ጠይቃ አታውቅም፣ ወደፊትም አትጠይቅም ያሉት ጀኔራል አበባው ብሔራዊ ጥቅሟን ከጥቃት የሚጠብቅ ሁለንተናዊ አቅም ያለው የመከላከያ ሠራዊት የመገንባት ጥረቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የሸኔ የሽብር ቡድንና የጽንፈኛው ኀይልን ወደ ሥርዓት ለመመለስ በተደረገው ጥረትም ከፍተኛ ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል።
በኀይል ፍላጎታቸውን ለማሳካት የሞከሩ ኀይሎች ህልም መምከኑን የገለጹት ጄኔራል አበባው ታደሰ ጽንፈኞች የቀራቸው ጉልበት በሚዲያ ላይ ሕዝቡን ማሸበር ብቻ መኾኑን ተናግረዋል።
በንግግር እና በተግባር መካከል ከፍተኛ ለውጥ መኖሩ እና በመሬት ላይ በተሠራው ውጤታማ ተግባር የጽንፈኞችን እና የተከፉይ ፕሮፓጋንዲስቶችን የሚዲያ ጫጫታ ማክሸፍ እንደተቻለም ጠቁመዋል።
ከወረዳ ያለፈ ሀሳብና ህልም የሌላቸው የሸኔ ቡድን እና የጽንፈኛው ኀይሎች ሕዝቡ ላይ በሚፈጽሙት ግፍ ከሕዝቡ ተነጥለው እርስ በእርሳቸው እየተገዳደሉ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
እነዚህ ኀይሎች የሎጅስቲክ፣ የመረጃ እና የሰው ኀይል እጥረት እንደገጠማቸው እና ቀጣይም በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን የማይሰጡትን እንዲሁም ተበታትነው የሚገኙትን ትንንሽ ቋጠሮዎችን የማጽዳት ተግባሩ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በሠራዊቱ እና በሕዝቡ ጥረት በአብዛኛው ቦታዎች ላይ የመጣውን ሰላም ለማስቀጠል በከፍተኛ የኀላፊነት ስሜት ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ሠራዊቱ የሚለካው በአስተሳሰቡና በስነልቦናው ጥንካሬ በመኾኑ በብዙ ፈተናዎች በጽናት ያለፈ ፤ ጠንካራ ዲሲፒሊን ያለው ፤ ግዳጅ የመፈፀም አቅም እና ሀገራዊ ፍቅር ያለው ሠራዊት መገንባት መቻሉንም አሥረድተዋል።
የመጨረሻ የኢትዮጵያ ምሽግ መኾኑን በተግባር ያስመሰከረው ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ጠላቶች የሚጮሁበት ጥንካሬውን ስለሚያውቁ ነው ብለዋል።
ጄኔራል አበባው ታደሰ በውድ መስዋዕትነት የመጣውን ሀገራዊ ለውጥ፣ ሕዝብ እና መንግሥት የሰጡትን አደራ በታላቅ ኀላፊነት የመወጣት ተግባሩን ሠራዊቱ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳለው ተመራቂዎች የበታች ሹም የኮማንዶ አመራሮችም በሚመደቡባቸው ክፍሎች በአርዓያነት እና በጀግንነት በመምራት እና የሀገር ሰላም እንዲሁም ብሔራዊ ጥቅም በማስጠበቅ ለትውልዱ የማሸጋገር ኀላፊነታቸውን በታላቅ ወታደራዊ ዲሲፒሊን እና ሀገራዊ ፍቅር እንዲወጡም አሳስበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!