
ደብረ ማርቆስ፡ ግንቦት 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከተማ አሥተዳደሩ የ2016 በጀት ዓመት የ10 ወራት የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎችን ገምግሟል፡፡
የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ መንበሩ ዘውዴ በአካባቢው የተከሰተው የሰላም እጦት የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎችን በታቀደው ልክ ማሳካት እንዳይቻል አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል ብለዋል፡፡
በችግር ውስጥም ኾኖ አበረታች የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ተግባራትን መፈጸም ተችሏል ነው ያሉት፡፡
በከተማ አሥተዳደሩ የመማር ማስተማር ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉን በጥንካሬ ያነሱት ከንቲባው የከተማዋ ገቢ አሠባሠብ ግን በዝቅተኛ አፈጻጸም ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ለመሠብሠብ ከታቀደው 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ውስጥ እስካሁን ማሳካት የተቻለው ከ22 በመቶ የማይበልጥ ነው ፡፡ በቀሪ ጊዜያት ይህንን አፈጻጸም ከፍ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
በከተማዋ ከ59 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጪ እየተሠሩ የሚገኙ የባዞላ እግረኛ መንገድ ንጣፍ፣ የአደባባይ ልማት እና የተፋሰስ ጥገና ተግባራት መዘግየት ቢታይባቸውም አፈጻጸማቸው ከ50 በመቶ በላይ በመኾኑ በቀሪ ጊዜያት ለማጠናቀቅ እየተሠራ ስለመኾኑም አመላክተዋል፡፡
የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ዘላቂ በማድረግ ያልተጠናቀቁ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎችን ለመፈጸም በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባም ከንቲባ መንበሩ ዘውዴ አሳስበዋል፡፡
ያጋጠሙ ፈተናዎችን በመሻገር የኅብረተሰቡን የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት ርብርብ እየተደረገ ነው ያሉት ደግሞ የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አብተው መኳንንት ናቸው፡፡
የጸጥታ ችግሩ በመንግሥት መዋቅር እና አሠራር ላይ ከፍተኛ ጫና ቢያሳድርም የከተማዋን ገጽታ የሚቀይሩ የልማት ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን ነው የተናገሩት። በተለይ ከሥራ ዕድል ፈጠራ አንጻር አበረታች ለውጥ መታየቱን ለአብነት አንስተዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ከ20 ሺህ ለሚበልጡ ሥራ ፈላጊዎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ወደ ተግባር የተገባ ሲኾን 92 በመቶ የሚኾኑ ሥራ ፈላጊዎችን በቋሚ እና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ሽፋንን ለማሳደግ በተሠራው ሥራ ከ29 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ 92 በመቶ ማሳካት ተችሏል ብለዋል፡፡
ሰላምን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የሚያስችሉ ተግባራትን ለማጠናከር በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
የደጃዝማች ተድላጓሉ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ መኮንን ደባሱ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን በማጠናከር ኅብረተሰቡ ያነሳቸውን ችግሮች ተቀራርቦ መፍታት የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ መኾኑን ነው ያመላከቱት፡፡
የሰላም እጦቱ ያስከተለውን ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ወድመት ተግቶ በመሥራት ማካካስ፤ ኅብረተሰቡን ያማረሩ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ መፍታት የቀጣይ ጊዜ ቁልፍ ተግባራት መኾናቸውም በግምገማ መድረኩ ላይ መግባባት ተደርሶባቸዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!