የከንቲባ ችሎት አገልግሎት የበርካታ ዓመታት የሕዝብ ጥያቄዎችን እየፈታ መኾኑን ተገልጋዮች ገለጹ።

19

ባሕር ዳር: ግንቦት 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ አሥተዳደር የከንቲባ ችሎት አገልግሎት የበርካታ ዓመታት የሕዝብ ጥያቄዎችን እየፈታ መኾኑን ተገልገዮች ገልጸዋል። ለበርካታ ዓመታት በመገፋፋት ሲንከባለሉ የነበሩ ጥያቄዎች በችሎቱ እየተመለሱ ነውም ብለዋል።

የችሎት አገልግሎቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ተገልጋዮቹ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። በችሎት አገልግሎቱ ተገልጋዮች ደስተኛ መኾናቸውንም ነው ያስገነዘቡት።

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባዩህ አቡሃይ እንደገለጹት በከንቲባ የችሎት አገልግሎት የዓመታት የሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ እየተሰጠ ነው።

የከንቲባ ችሎት በአጋጣሚ የተጀመረ ሳይኾን ጎንደር በነበራት ወርቃማ የታሪክ ዘመን ላይ የዙፋን ችሎት ይስጥ እንደነበር አንስተዋል። ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የታችኛው የሥልጣን እርከን የማይፈታቸውን ሀገራዊ ጉዳዮች ይዘው የድሮ ነገስታቶች የዙፋን ችሎት በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ያስችሉ እንደነበር ታሪክ እንዳለ አንስተዋል።

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ወደ ከንቲባ ችሎት የሚመጡ ባለጉዳዮች ጥናት እንዲጠና በማድረግና ተሞክሮዎችን ከሌላ ቦታ በመውሰድ እንዲሁም ሕዝቡ በተለያዩ መድረኮች ያነሳቸውን የመልካም አሥተዳደር ችግሮች ለመፍታት ያለመ የከንቲባ ችሎት መጀመሩን ገልጸዋል።

እስካሁን ለ5ኛ ጊዜ የከንቲባ ችሎት የተካሄደ ሲኾን በርካታ ችግሮችን መፍታቱን የገለጹት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በግለሰብ ደረጃ ከ330 በላይ ባለጉዳዮች ጉዳያቸው ስለመታየቱ ነው የተናገሩት።

በችሎቱ 270 የሚኾኑት ጉዳዮች ምላሽ ያገኙ ሲኾን ቀሪዎቹ ቀጠሮ ላይ መኾናቸውን ገልጸዋል።

የብዙ አቅመ ደካሞችን እንባ እያበሰ ያለ የችሎት አገልግሎት ስለመኾኑም አስገንዝበዋል። የሕዝብን የመልካም አሥተዳደር ችግር የቀረፈም ነው ብለዋል።

የችሎት አገልግሎቱ ከቀበሌ ጀምሮ የማይፈቱት ወደ ክፍለ ከተማ ከዛም አልፎ ምላሽ ያላገኙ ወደ ሥራ አሥኪያጅ ችሎት በመታየት ካልተፈታ በከንቲባ ችሎት የሚመለከተው አመራር እና ባለሙያ ፊት ለፊት ከባለጉዳዮች ጋር የሚገናኙበት በመኾኑ ግልጽነት፣ ተጠያቂነት፣ ብልሹ አሠራርን የሚያስቀር መኾኑን ነው የተናገሩት።

የፍርድ ቤቶችን ጫና የሚቀንስ፣ የዜጎችን የዘመናት ጥያቄ ምላሽ እየሰጠ የሚገኝ የችሎት አገልግሎት መኾኑንም ገልጸዋል ።

ተጀምሮ የሚቋረጥ ሳይኾን ያለምንም መቆራረጥ ቀጣይነት ባለው መንገድ እስከታች የተጀመረውን አገልግሎት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው የተናገሩት።

የጎንደር ከተማ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳሰፈረው ኅብረተሰቡ በየደረጃው የሚሰጠውን የችሎት አገልግሎት መደገፍ፣ ማበረታታት እና ተባባሪ በመኾን ትክክለኛ መረጃ ማቅረብ እንደሚገባው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አሳስበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአፍሪካዊያን ቀን!
Next articleየአዘዞ -አርበኞች አደባባይ የመንገድ ፕሮጀክት ቀሪ የአስፓልት ንጣፍ ሥራን ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው።