
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአፍሪካዊያን የነፃነት ቀን እውን ይኾን ዘንድ ከጦር ሜዳ ገድል እስከ ዲፕሎማሲ ትግል አያሌ መስዋዕትነት ተከፍሎለታል፡፡ ፍትሕ በራቀው የዓለም አደባባይ ላይ ብቻዋን ከፍ ብላ ቆማ ዘለግ ያለ የነፃነትን ነጋሪት የምትጎስመው ሀገር ይኽ ቀን እንደሚመጣ ቀድማ ያወቀች ትመስላለች፡፡ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን “ይቻላል” ትናንት ብቻ ሳይኾን ያኔም ‘ሞቷቸው’ ነበር፡፡
የነፃነት ድምጿ እና ግርማ ሞገሷ እንደ ኢያሪኮ የቅኝ ግዛት ግንብን ያፈራረሰው ኢትዮጵያ እንደ ሙሴ መርታ እና እንደ ዳዊት ተፋልማ ነፃ ሀገር ብቻ ሳይኾን ነፃ አህጉርም መመሥረት ችላለች፡፡ ከችግሮች በላይ የኾነ ጽናት፣ ከመሰናክል በላይ የወጣ ብስለት፣ ከጀብደኝነት የራቀ ድፍረት እና ከመታበይ የፀዳ ማንነት በአፍሪካ አንድነት ድርጅት የምሥረታ ወቅት ኢትዮጵያ ላይ ተስተውሏል፡፡ “አህጉራዊ ችግሮቻችን አፍሪካዊ ምላሽ ብቻ ያሻቸዋል” ወፍ ዘራሽ ዝማሬ ሳይኾን ዘመን ተሻጋሪ እሳቤ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ፍትሕ በተጓደለበት እና ባርነት ባጠላበት የጨለማ ዘመን የነፃነት ፋና ወጊ ቀንዲል ኾና የታየች ሀገር ናት፡፡ በባርነት ወቅያኖስ ውስጥ ለሰጠሙት አፍሪካዊያን የነጻነት መርከብ፤ የቅኝ ግዛት ሰንሰለትን የበጣጠሰች የነፃዋ አህጉር ምስረታ መልህቅ ማረፊያ ወደብ ናት፡፡ ከማንዴላ እስከ ሙጋቤ፤ ከሴኩቱሬ እስከ ነሬሬ ስለኢትዮጵያ አፍሪካዊ ዋጋ ብዙ ብለዋል፡፡
የምስረታው እውን መኾን ከህልም በላይም ቅዥት ነው የተባለለት እና ሐምሌ 2/1995 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ደርባን ወደ አፍሪካ ኅብረት ሥያሜውን የቀየረው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምሥረታው ልክ በዛሬዋ ቀን በመዲናችን አዲስ አበባ ነበር፡፡ ቅኝ ግዛት ካስከተለው ምዝበራ በላይ ጥሎት ያለፈው የሥነ ልቦና ስብራት በቀላሉ የሚሽር አልነበረም፡፡ ነፃዋ ሀገር ኢትዮጵያ ባትኖር ነፃዋን አህጉር የሚያበሥረው የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን መመሥረት ቀርቶ ማስብ እንኳን የሚቻል አልነበረም፡፡
ሃጋይ አርሌክስ ስለ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ግለ ታሪክ በጻፈው መጽሐፉ “ድህረ-ቅኝ ግዛት ለአፍሪካ ሀገራት የባሰ ጨለማ ኾኖ ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ እና ንጉሠ ነገሥቱ ባይኖሩ ኖሮ አፍሪካዊያን ማንሰራራት ባልቻሉም ነበር” ይሉናል፡፡ በወቅቱ ነፃነታቸውን ዘግይተው የተጎናጸፉ ሀገራት በሚከተሉት የድህረ ቅኝ ግዛት ፖሊሲ ምክንያት አንዱ ሀገር ሌላኛውን ሀገር በመንቀፍ ለኅብረት ቀርቶ ለመጎራበት እንኳን ተቸግረው ነበር፡፡
የወቅቱን ፖለቲካዊ የጎራ አሰላለፍ ቃኝታ ከቅኝ ግዛት ቀንበር ነፃ የወጡ ሀገራትን አስተባብሮ እና አሰባስቦ ነፃ አህጉር መመሥረት ዘላቂ መፍትሄ መኾኑን ያየችው ኢትዮጵያ አድካሚውን እና ውስብስቡን ኅብረት እውን ለማድረግ ጉዞ ጀመረች፡፡ ምዕራባዊያኑ ህልም ያሉትን ኅብረት ለመመሥረት ኢትዮጵያ የጀመረችው ትልም ፈተናዎች የገጠሙት ግን ከውጭ ሳይኾን ከውስጥ ነበር፡፡ ወቅቱ ከቅኝ ግዛት ቀንበር ነፃ የወጡ 31 የአፍሪካ ሀገራት ቢኖሩም በመጻዒዋ ነፃ አፍሪካን በመመሥረት ሂደት በሁለት ዋና ዋና ጎራዎች ተከፈሉ፤ ካዛብላንካ እና ሞኖሮቪያ በሚል፡፡
የተለያዩትን ሰብስባ፣ የተበተኑትን አንድ አድርጋ እና የተኮራረፉትን አቀራርባ ነፃ አህጉር እውን የማድረጉ ኅላፊነት የወደቀው በነፃዋ ሀገር ኢትዮጵያ ትከሻ ላይ ነበር፡፡ ኤርሚያስ ጉልላት “ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ እና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምሥረታ” በሚለው መጽሐፋቸው ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የተቃጣባትን የቅኝ ግዛት ሙከራ በጀግንነት አክሽፋ ብቸኛዋ ቅኝ ያልተገዛች ሀገር በመሆኗ ሁሉም ነፃ የወጡ ሀገራት ኢትዮጵያን መያዝ ይፈልጉ ነበር ይሉናል፡፡ በየአካባቢው በሚደረግ የነፃዋ አህጉር ምስረታ ምክክር ላይ እንድትገኝም ግብዣ ይደርሳት እንደነበር ያነሳሉ፡፡
አፍሪካ በፖለቲካ እና በምጣኔ ሃብት ራሷን መቻል አለባት ለዚህም ሀገራቱ በኮንፌዴሬሽን አንድ መኾን አለባቸው የሚል አቋም የሚያራምዱት የካዛብላንካ ቡድን እና በሌላ ጎራ አፍሪካ ከገባችበት ምጣኔ ሃብታዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ ለመውጣት የሌሎች ሀገራት እና አህጉራት ድጋፍ ያስፈልጋታል የሚል አቋም ያላቸው የሞኖሮቪያ ቡድን አባላት 22 ሀገራት ነበሩ፡፡
ኢትዮጵያ የምትፈልገው አህጉራዊ ኅብረት ይመጣ ዘንድ ሁለቱ ቡድኖች የያዟቸውን ልዩነቶች አጥብበው ወደ አንድ መምጣት ነበረባቸው፡፡ ኤርሚያስ ጉልላት እንደሚሉት ኢትዮጵያ 1954 ዓ.ም ላይ ከሁለቱም ጎራዎች የተሳትፎ ጥሪ ቢቀርብላትም የቀጣዩን አንድነት ለማምጣት እንዲቻል የካዛብላንካውን ቡድን መርጣ ናይጀሪያ ሌጎስ ላይ ተገኘች፡፡ በስብሰባው ቀጣዩ ስብሰባ አዲስ አበባ እንዲኾን ግብዣ አቅርበው ተመለሱ፡፡ ከብዙ ውጣ ውረድ እና ማሳመን በኋላ በ1955 ዓ.ም ግንቦት ወር አጋማሽ ላይ 31 ነፃ የአፍሪካ ሀገራት የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ለመመሥረት አዲስ አበባ ላይ ለመገናኘት ቀነ ቀጠሮ ያዙ፡፡
ከዲፕሎማሲያዊ ጥረት ጎን ለጎን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መሰብሰቢያ አዳራሽን የገነባችው ኢትዮጵያ በተለየ ድምቀት መሪዎቹን ተቀብላ ስብሰባውን አስጀመረች፡፡ መሪዎቹ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ስብሰባውን እንዲመሩ በሙሉ ድምጽ በመምረጣቸው ሰብሰባውን በታሪካዊ የመክፈቻ ንግግራቸው አስጀመሩ፡፡ “ታሪክ ሕያው ምስክር ነው፤ ይኽ ቀን የአፍሪካዊያን ቀን ተብሎ ይከበራል” ሲሉ ተደመጡ፡፡
በመጨረሻም የአፍሪካ መሪዎች የአንድነት መተዳደሪያ ቻርተርን ተፈራረሙ፡፡ ቻርተሩም በአማርኛ፣ በአረብኛ፣ በፈረንሳይኛ እና በእንግሊዝኛ ተዘጋጅቶ ታተመ፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታም እውን ኾነ፡፡ በምስረታው የተዘባበቱ ሁሉ ዐይን እና ጆሯቸውን አዲስ አበባ ላይ ተከሉ፡፡ አድካሚው የአንድነት እና የኅብረት ጉዞ በድል ተጠናቆ ምስረታው እውን ኾነ፡፡
በኢትዮጵያ ማመን እና ኢትዮጵያን መከተል ዝም ብሎ የመጣ ተዓምር አይደለም፡፡ ከመሪው እስከ ተመሪው ለሀገር ክብር ቅድሚያ መስጠቱ ተናግራ የምትሰማ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሀገር ለመፍጠር እንደተቻለ በርካቶች አሁንም ድረስ ይስማማሉ፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!