አሁን ላይ አንጻራዊ ሰላም በመምጣቱ የግብር አከፋፈሉ መሻሻል ማሳየቱን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ገለጸ።

37

ባሕር ዳር: ግንቦት 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ማኅበራዊ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት ማኅበረሰቡ ግብር የመክፈል ግዴታውን እንዲወጣ የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ጠይቋል። የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኀላፊ ክብረት ማሕሙድ እንዳሉት በአማራ ክልል በ2016 በጀት ዓመት ከከተማ አገልግሎት እና በመደበኛ ግብር 71 ነጥብ 65 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ነበር።

ባለፉት አሥር ወራትም 32 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ብቻ መሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል። ይህም በአስር ወሩ መሰብሰብ ከነበረበት 54 በመቶ ብቻ መፈጸሙን ገልጸዋል። በክልሉ የምዕራቡ አካባቢ በተለይም ደግም ከደቡብ ጎንደር እስከ ምሥራቅ ጎጃም የሚገኙ ዞኖች እና ከተማ አሥተዳደሮች አፈጻጸማቸው ዝቅተኛ መኾኑን አንስተዋል። ለዚህ ደግሞ የሰላም እጦቱ በታሰበው መጠን መሰብሰብ እንዳይቻል አድርጎታል ነው ያሉት፡፡

የአፈጻጸሙ ዝቅተኛ መኾን ማኅበረሰቡ የሚያነሳቸው የልማት እና የማኅበራዊ አገልግሎት ሥራዎች ላይ የፋይናንስ ግብዓት ለማቅረብ ፈታኝ አድርጎታል ነው ያሉት። አሁን ላይ መንግሥት በወሰደው ሰላምን የማረጋገጥ ሥራ አንጻራዊ ሰላም በመምጣቱ የግብር አከፋፈሉ መሻሻል ማሳየቱን ገልጸዋል። ግብር ከፋዮች የሚጠበቅባቸውን ግብር እንዲከፍሉም ጠይቀዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየፈተና ጥሪ ማስታወቂያ
Next articleየአፍሪካዊያን ቀን!