“በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር እየተሻሻለ መምጣቱን ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።

91

ባሕር ዳር: ግንቦት 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ጠብቆ የማፅናት ጉዳይ የሁሉም ኀላፊነት ሊኾን እንደሚገባ በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ ገልጿል። ቦርዱ ይህንን የገለጸው ባሕርዳር በመገኘት ከክልሉ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ ከባሕርዳር እና ጎንደር የኮማንድ ፖስት ዕዝ ኀላፊዎች እንዲሁም በተፈጠረው የሰላም መደፍረስ ተጠርጥረው በባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ማረሚያ ቤት ከሚገኙ ተጠርጣሪዎች ጋር ባደረገው የውይይት መድረክ ላይ ነው።

የመርማሪ ቦርዱ ሠብሣቢ አዝመራ አንዴሞ የየትኛውንም ማኅበረሰብ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፓለቲካዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ እንዲቻል በመጀመሪያ የአካባቢው ሰላም እና ጸጥታ እንዲሁም የሕግ የበላይነት መረጋገጥ እንዳለበት ገልጸዋል ። ከሰብዓዊ አያያዝ አንጻር በማረሚያ ማዕከሉ የሚገኙ ተጠርጣሪዎች በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኙ መኾናቸውን መታዘባቸውን ተናግረዋል። ተጠርጣሪዎቹ ያነሷቸውን የተለያዩ ጥያቄዎች በመያዝ ለሚመለከታቸው አካላት በማቅረብ አፋጣኝ መፍትሔ እንዲያገኙ ለማድረግ ቦርዱ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራም ሠብሣቢው አስገንዝበዋል።

የቦርዱ አባል መስፍን እርከቤ ሰላም እንደ ሀገርም ይሁን እንደግለሰብ ለሚታቀዱ የእድገት እና የብልጽግና ጉዞዎች መሳካት መሠረት በመኾኑ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ቅድሚያ ሰጥቶ ሊጠብቀው የሚገባው ነው ብለዋል። የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በበኩላቸው የክልሉን ሰላም እና ጸጥታ የተሻለ ለማድረግ በተደጋጋሚ ከሕዝብ ጋር የውይይት መድረክ እየተደረገ እንደኾነ አንስተዋል። ርእሰ መሥተዳድሩ በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር እየተሻሻለ መምጣቱን አስገንዝበዋል። በአሁኑ ወቅትም ከኅብረተሰቡ ጋር በመኾን የተለያዩ መደበኛ ልማታዊ እና አሥተዳደራዊ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳለው የሰሜን ምዕራብ አማራ ኮማንድ ፖስት ሠብሣቢ ብርጋዴል ጄኔራል ዋኘው አለሜ እና የባሕርዳር አካባቢ ኮማንድ ፖስት ኀላፊ ሜጀር ጄኔራል መሰለ በለጠ በኮማንድ ፖስቱ ስር የሚገኙ አካባቢዎችን ዘላቂ ሰላም ከማረጋገጥ አኳያ ኅብረተሰቡ የራሱን ሰላም እና ጸጥታ እንዲጠብቅ የማደራጀት ሥራ እና መዋቅሮችን በመዘርጋት ሥልጠናዎች እየተሰጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሚዳ እምርታ የተሰኘ ኘሮጀክት ለብዙዎች የሥራ ዕድል የፈጠረ ፕሮጀክት ነው” አቶ አሰፋ መንግሥቱ
Next articleየፈተና ጥሪ ማስታወቂያ