የጸጥታ ችግሩ የኤች አይቪ ኤድስ ስርጭት እንዲስፋፋ እያደረገ መኾኑ ተመላከተ፡፡

28

ባሕር ዳር: ግንቦት 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ከአማራ ክልል ለተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች እና የማኅበረሰብ መሪዎች በወቅታዊ የኤች አይቪ ኤድስ ሁኔታ እና ምላሽ ላይ የንቅናቄ መድረክ እና ሥልጠና ተካሂዷል፡፡ በመድረኩ በየጊዜው እየተፈጠሩ ያሉ የጸጥታ ችግሮች የኤች አይቪ ኤድስ ስርጭት እንዲስፋፋ እያደረጉ መኾኑ ተመላክቷል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የባሕር ዳር ሀገረ ሰብክት ጸሐፊ መላከ ብርሃን ፍስሃ ጥላሁን ቀደም ሲል የሃይማኖት ተቋማት ስለ ኤች አይቪ ኤድስ ግንዛቤ እንዲኖር ሃይማኖቱ በሚያዝዘው መሠረት ሲሠሩ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ በተሠራው ሥራም መታመምም፣ መሞትም ቀንሶ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ አሁን አሁን በወቅታዊ ጫና በተፈጠረው መዘናጋት ስለ ቫይረሱ የሚሰጠው ትምህርት ቀንሷል ነው ያሉት፡፡ የሃይማኖት አባቶች ትልቁ አስተምህሯችን ሕዝብን ማዳን ነው ያሉት መላከ ብርሃን ሕዝብ ከሌለ ሃይማኖት አይኖርም፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አንድ ወንድ በአንዲት ሴት፣ አንዲት ሴትም በአንድ ወንድ ብቻ እንዲወሰኑ በጥብቅ ታስተምራለች ነው ያሉት፡፡

ሃይማኖቱ የሚያዝዘውን መፈጸም አንድም ለነፍስ ሁለትም ለስጋ ያድናል ብለዋል፡፡ አባቶች በተለይም አሁን ላይ ሰዎች እንዲወሰኑ እና ሕግጋትን እንዲያከብሩ ማስተማር ይገባናል ነው ያሉት፡፡ ከተፈጠረው መዘናጋት በአስቸኳይ በመንቃት ማስተማር እና ሕዝብን ማዳን እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡

የታመሙትንም መጠየቅ፣ አለማግለል እና መንከባከብ ይገባል ብለዋል፡፡ መድኃኒት የሚወስዱ ወገኖችም መድኃኒታቸውን በአግባቡ እየወሰዱ ሃይማኖታዊ ሥርዓትን መፈጸም እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት የነፍስ አባት እና የነፍስ ልጅ ግንኙነት መኖሩን የተናገሩት መላከ ብርሃን አባቶች ልጆቻቸውን በየጊዜው ስለሚያገኟቸው በሚገባ ማስተማር እንደሚችሉም ገልጸዋል፡፡

የባሕር ዳር ከተማ ዑለማ ምክር ቤት አባል ሼሕ ከድር መሐመድ ባለፉት ዓመታት የነበሩ የጸጥታ ችግሮች ለኤች አይቪ ኤድስ የነበረውን ትኩረት ቀንሶታል ብለዋል፡፡ አሁን ላይ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ደርሷል፤ በጋራ በመሥራት ሕይዎትን መታደግ ይገባል ነው ያሉት፡፡ ወጣቶች ኒካ ከማሰራቸው አስቀድሞ ራሳቸውን ማወቅ እንደሚገባቸውም አሳስበዋል፡፡ ራስን ሳያውቁ ጋብቻ መፈጸም ለአደጋ እያጋለጠ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ በቫይረሱ የተያዙ ወገኖችን መደገፍ፣ መንከባከብ፣ ማበረታታት፣ መጠየቅ ሃይማኖታዊም፣ ሰብዓዊም ግዴታ ነው ብለዋል፡፡ የሃይማኖት አባቶች እና አማኞች ቫይረሱ ያለባቸውን ወገኖች እንዲንከባከቡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በተለይም ሀገር ተረካቢ እና ነገ ብዙ ተስፋ ያላቸው ወጣቶች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡ ወጣቶች ራሳቸውን ለበሽታ ሳያጋልጡ ወደፊት ለሚጠበቅባቸው አደራ ዝግጁ መኾን እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል፡፡ በጎንደር አዘዞ የሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተክርስቲያን የመሪዎች ስብስባ አባል ወንጌላዊ ያዛቸው ደሴ የእግዚአብሔር ቃል ሰዎች እንዲወሰኑ ያዝዛል፤ ይሄን አስተምህሮ ለአማኞች በሚገባ ማስተማር ይገባል ነው ያሉት፡፡ ቫይረሱ በደማቸው የሚገኙ ወገኖችን መንከባከብ፣ መደገፍ፣ ማጽናናት መድኃኒታቸውን እንዲወስዱ ማበረታታት ይገባል ብለዋል፡፡ የሃይማኖት አባቶች እንደ አባትም እንደ ዜጋም ኀላፊነት አለባቸው ነው ያሉት፡፡

በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የኤች አይቪ ኤድስ ክትትል እና ግምገማ ባለሙያ መንግሥቱ መንገሻ በክልሉ ያለው የኤች አይቪ ስርጭት ከፍተኛ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ባለፉት ዓመታት የተፈጠሩ ግጭቶች እና መፈናቀሎች የኤች አይቪ ኤድሰ ስርጭት እንዲሰፋ አድርጓል ነው ያሉት፡፡ በግጭት ወቅት አስገድዶ መደፈር እና ሌሎች ፆታዊ ጥቃቶች እንደሚኖሩ የተናገሩት ባለሙያው እንዲህ ዓይነት ሂደቶች ስርጭቱ እንዲሰፋ እያደረጉ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡

በግጭት ምክንያት ያቀዱት አልሳካ ሲል እና ሕይዎት አስቸጋሪ ስትኾን ሰዎች ተስፋ እንደሚቆርጡ እና ጥንቃቄ የጎደለው ግንኙነት እንደሚያደርጉም ተናግረዋል፡፡ በግጭት ምክንያት በሚኖረው መፈናቀል እና የኑሮ ደረጃ መቀነስ ላልተፈለገ ሥራ እንደሚያጋልጥም አንስተዋል፡፡ በክልሉ የተፈጠሩ ተደጋጋሚ ግጭቶች እና ሌሎች ችግሮች በክልሉ የኤች አይቪ ስርጭት እንዲሰፋ አድርጓል ነው ያሉት፡፡ ማግለል እና አድሎ አሁንም በስፋት መኖሩንም አመላክተዋል፡፡ ውይይቶችን ማድረግ፣ ግንዛቤ ማስጨበጥ እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል፡፡

በአማራ ክልል 175 ሺህ 955 ወገኖች በኤች አይ ቪ ኤድስ ተይዘዋል። በአማራ ክልል የስርጭት ምጣኔ 1 ነጥብ 09 በመቶ ነው፤ ይኽም በጤና አጠራር ወረርሽኝ ነው። በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ 0 ነጥብ 9 ነው ተብሏል። የክልሉ ስርጭት ከሀገር አቀፉ እንደሚልቅም አንስተዋል፡፡ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች እያመጡት ያለው ለውጥ አዝጋሚ እና ዝቅተኛ መኾኑንም ገልጸዋል። አሁንም እንደ አዲስ በኤች አይ ቪ የሚያዙ ወገኖች መኖራቸው ተመላክቷል። በአፍላ የወጣትነት እድሜ ያሉ እና ሠርተው ራሳቸውን እና ሀገራቸውን የሚለውጡ ወገኖች ሰለባ እየኾኑ ነው ተብሏል። ኤች አይቪ ኤድስን ለመከላከል ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንደሚገባውም አሳስበዋል፡፡

የጤና ሚኒስቴር ተወካይ ሐብታሙ ካሳ የሃይማኖት አባቶች የችግር መውጫ መንገዱን በማመላከት በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ የኤች አይቪ ኤድስ ስርጭት እየቀነሰ ቢኾንም አሁንም ስርጭቱ በስፋት ያለባቸው ክልሎች እና ከተማ አሥተዳደሮች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል የአማራ ክልል አንደኛው መኾኑን አንስተዋል፡፡

የሃይማኖት ተቋማት እና የማኅበረሰብ መሪዎች ባለፉት ዓመታት ለተሠሩት ሥራዎች ትልቅ አስተዋጽኦ እንደነበራቸው ነው የተናገሩት፡፡ አሁን አሁን በሚፈጠሩ ግጭቶች አስተዋጽኦአቸው መቀነሱንም አመላክተዋል፡፡ ሰላምን በማጽናት የጤና ሥርዓቱን ማስተካከል እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡ በተለይም ለሴቶች እና ለሕጻናት ሰላም ያስፈልጋል፤ ሰላም በሌለ ጊዜ ከባድ ችግር እየተከተላቸው ነው ብለዋል፡፡ የሃይማኖት አባቶች አማኞቻቸውን በመጠበቅ የምድር እና የሰማይ ኀላፊነታቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በመማር ማስተማሩ ዙሪያ ቀሪ ሥራዎችን በቀሪ ጊዜያት መፈጸም እና ለሚቀጥለው ዓመት ግብዓት መያዝ ይገባል” ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)
Next article“ሚዳ እምርታ የተሰኘ ኘሮጀክት ለብዙዎች የሥራ ዕድል የፈጠረ ፕሮጀክት ነው” አቶ አሰፋ መንግሥቱ