“በመማር ማስተማሩ ዙሪያ ቀሪ ሥራዎችን በቀሪ ጊዜያት መፈጸም እና ለሚቀጥለው ዓመት ግብዓት መያዝ ይገባል” ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)

38

ባሕር ዳር: ግንቦት 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ከሰሜን ጎጃም እና ባሕር ዳር ከተማ ትምህርት መምሪያ የትምህርት መሪዎች ጋር በበጀት ዓመቱ የዘጠኝ ወር የሥራ አፈጻጸምን ገምግሟል። በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኅላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) በመክፈቻ ንግግራቸው የተሠሩ መልካም ሥራዎች እንዳሉ እና በቀጣይ ቀሪ ሥራዎችንም ለመፈጸምና ለሚቀጥለው ዓመት ግብዓት እንደሚያዝበት ገልጸዋል።

ለትምህርት ተቋማት በተደረገ ድጋፍ እና ክትትል የተገኙ ጥንካሬ እና ውስንነቶች በቀጣይ የሚስተካከሉበትን ዕድል ማየት እንደሚገባ አሳስበዋል። በሚቀጥለው የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሥራ ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ ውይይቱ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል። የ6ኛ፣ 8ኛ እና 12ኛ ክፍሎችን ለማስፈተን እና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ዕቅድ መያዙን እና ለዚህም የትምህርት መዋቅሩ አቅዶ እና ተዘጋጅቶ መሥራት እንዳለበት ገልጸዋል። በተፈጠረው የሰላም ችግር የተፈጠረውን መፋዘዝ ቀርፎ ወደ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራ ለመግባት በክረምቱ የሚሠሩ ሥራዎች መኖራቸውንም ገልጸዋል።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ኃይለማርያም እሸቴ በሰላም ችግር ምክንያት በትምህርት ላይ ተጽዕኖ መፈጠሩን ገልጸዋል። በከተማ አሥተዳደሩ ከመቶ በላይ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ሁለት የሁለተኛ ደረጃ እና 22 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሥራ ማቆማቸውን ጠቅሰዋል። ተማሪዎችም በሥነ ልቦና መጎዳታቸውን ተናግረዋል።

በቀሪ ትምህርት ቤቶች ግን የ6ኛ፣ የ8ኛ እና የ12ኛ ክፍል ተፈታኞችን የማዘጋጀት ሥራ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል። አቶ ኃይለማርያም ተፈታኞችን በዕውቀት፣ በሥነ ልቦና እና በፈተና አወሳሰዱ ላይ የማዘጋጀት ሥራ እየተሠራ መኾኑን ጠቅሰዋል። የሰሜን ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ተወካይ ኀላፊ አትርሳው ጌትነት በዞኑ በሰላም እጦት ምክንያት ከ468 አንደኛ ደረጃ እና 34 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ትምህርት መስጠት የተቻለው በባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ ብቻ መኾኑን ገልጸዋል። በዚህም 14 ሺህ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ መኾናቸውን ተናግረዋል። በቀጣይ የሚሰጠውን ፈተና የሚወስዱት ተማሪዎችም የዚሁ ወረዳ ተማሪዎች ብቻ መኾናቸውን ጠቅሰዋል።

በውይይቱ የክልሉ የትምህርት ሥራ አፈጻጸም ሪፖርት እና የድጋፍ እና ክትትል ግብረ መልስ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል። የ12ኛ ክፍል ተፈታኞችን ለማዘጋጀት በሚቻልበት ሁኔታ ላይም ምክክር ተደርጓል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከየትኛውም የሀገራችን አቅጣጫ የሚመጡ ጥቃቶችን ለመመከት የሚያስችል የተሟላ ወታደራዊ ቁመና ተገንብቷል” ጄኔራል አበባው ታደሰ
Next articleየጸጥታ ችግሩ የኤች አይቪ ኤድስ ስርጭት እንዲስፋፋ እያደረገ መኾኑ ተመላከተ፡፡