
ባሕር ዳር: ግንቦት 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኮማንዶ እና አየር ወለድ ዕዝ ማሠልጠኛ ማዕከል ከዕዙ የተለያዩ ክፍሎች በመመልመል በአመራር ትምህርት ቤቱ ያሠለጠናቸውን ሁለተኛ ዙር የበታች ሹም መሪዎችን አስመርቋል። በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የጦር ኀይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ የሀገራችንን ዕድገት የማይፈልጉ ኀይሎች በራሳቸው ያቃታቸውን ጽንፈኞችን በማሰማራት ሀገራችንን ለመበታተን መሞከራውን ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን በጀግናው ሠራዊታችን እና በአስተዋዩ ሕዝባችን ድጋፍ ህልማቸው እንዲመክን መደረጉን ገልጸዋል።
ጄኔራል አበባው “ሀገራችንን በተለያየ አቅጣጫ ለመወጠር ሞክረው የነበሩ ኀይሎችን ስጋት ወደማይኾኑበት ደረጃ አድርሰናል” ብለዋል፡፡ ሀገራችንን ለማጽናት በተከፈለው ውድ ዋጋ የመጣውን ሰላም ለማረጋገጥ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙ ጄኔራል አበባው ጠቁመዋል፡፡ ከየትኛውም የሀገራችን አቅጣጫ የሚመጡ ጥቃቶችን ለመመከት የሚያስችል የተሟላ ወታደራዊ ቁመና ተገንብቶ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ተመራቂ የበታች ሹም መሪዎችም ያገኙትን አቅም ወደየሚመደቡባቸው ቦታዎች በመተግበር ኀላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል። በዝግጅቱ ላይ ተመራቂዎች የተለያዩ ወታደራዊ ትርዒቶችን ማሳየታቸውን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!