
ባሕር ዳር: ግንቦት 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የእንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ዘርፉን ምርታማነት ማሳደግ እንደሚገባ የአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት ገልጿል፡፡ ጽሕፈት ቤቱ ዛሬ በደብረ ብርሃን ከተማ የእንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ፓኬጅ የአሠልጣኞች ሥልጠና አስጀምሯል፡፡
የአማራ ክልል እንሰሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት ምክትል ኀላፊ ነጋ ይስማው አሁን ላይ በአዲስ መልክ የተዘጋጀው ፓኬጁ ዘርፉ አሁን ያለበትን የእድገት፣ የአቅርቦት እና የፍላጎት ደረጃ በማገናዘብ ለማሳደግ ነው ብለዋል፡፡ በእንስሳት እና ዓሣ ሃብት ላይ ተሳታፊ የኾኑ አርሶ አደሮች እና ኢንተርፕራይዞች በኢኮኖሚ ማደግ መጀመራቸው፣ ምርቱን የመጠቀም ፍላጎት መጨመሩ፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ጉልህ አማራጭ መኾኑን እና የውጭ ምንዛሬን ለማስገኘት አንዱ አቅም ኾኖ መገኘቱ ፓኬጁን በአዲስ መልክ አዘጋጅቶ መስጠት አስፈልጓል ብለዋል አቶ ነጋ፡፡
ሥልጠናው ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ 3 ቀናት የሚሰጥ ሲኾን ከወረዳ እና ከዞን የተውጣጡ ባለሙያዎች እና የሥራ ኀላፊዎች ይታደሙበታል ተብሏል፡፡
ዘጋቢ፡- ፋንታነሽ መሀመድ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!