
ወልድያ: ግንቦት 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በሰሜን ወሎ ዞን ትርፍ የሚጭኑ እና ከታሪፍ በላይ የሚያስከፍሉ አሽከርካሪዎችን መቆጣጠር የሚያስችል በቴክኖሎጅ የታገዘ የኢ- ትኬቲንግ ሲስተም አገልግሎትን ለማስጀመር እየተሠራ እንደኾነ ተገልጿል፡፡ በአካባቢው ያለውን የትራንስፖርት አገልግሎት ውጤታማ ለማድረግ በወልዲያ መናኾሪያ መቆጣጠሪያውን ለማስጀመር ዝግጅት መጠናቀቁን የዞኑ ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ባንቴ ምሥጋናው ተናግረዋል።
በአማራ ክልል በተመረጡ 11 መናኾሪያዎች አገልግሎቱ መጀመሩን የገለጹት “የሁሉም ትኬት” መሥራች እና ዋና ሥራ አሥኪያጅ ካሊድ አህመድ የኢ-ቲኬቲንግ አሠራር ተጓዦች ያለእንግልት ባሉበት በእጅ ስልካቸው ትኬት መቁረጥ እንዲችሉ ያግዛል ብለዋል፡፡ ለባለሃብቶችም አዋጭ መኾኑን አስረድተዋል።
የግዳን ወረዳ ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ንጉሴ አበባው እና የጋሸና ከተማ አሥተዳደር የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ገዳሙ ተገኘ በቴክኖሎጅ የታገዘ የኢ- ትኬቲንግ አገልግሎት መጀመሩ የትራንስፖርት አገልግሎት ችግሩን በመፍታት የኅብረተሰቡን ችግር ያቃልላል ብለዋል።
አገልግሎቱ የተሳካ እንዲኾን የክልሉ ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክ ባለሥልጣን ላደረገላቸው ድጋፍ ምሥጋና አቅርበዋል። የትራንስፖርት ዘርፉን በአግባቡ በመምራት የኢ -ትኬቲንግ አገልግሎቱ ውጤታማ እንዲኾን በትኩረት እንደሚሠራ የተናገሩት ደግሞ የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዱባለ አብራሬ ናቸው። የሰሜን ወሎ ዞን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ የዞኑን ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክ ጽሕፈት ቤት ጠቅሶ እንዳለው በዞኑ 855 አነስተኛ እና መለስተኛ የሕዝብ ተሽከርካሪዎች ይገኛሉ።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!