
ባሕር ዳር: ግንቦት 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ አፍሪካ በዓለም ሰላም እና ደኅንነት ሚናዋን እንድትወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በተመድ የፀጥታ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ንግግር ያደረጉት አንቶኒዮ ጉተሬዝ የአፍሪካን ተሳትፎ እና አመራር በዓለም አቀፍ የሰላም እና የፀጥታ መዋቅር ውስጥ ማካተት ያስፈልጋል ብለዋል።
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤትን ጨምሮ የዓለም አቀፍ አስተዳደር ዘዴዎች የተነደፉት በወቅቱ ብዙ የአፍሪካ ሀገራት የቅኝ ግዛትን ሰንሰለት በመጣል ላይ በነበሩበት ወቅት እንደነበር አስታውሰዋል። “ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ማግስት ጀምሮ ዓለም ቢለወጥም ዓለም አቀፍ ተቋማት ግን ባሉበት ናቸው” ብለዋል።
በፀጥታው ምክር ቤት አፍሪካ ዓለም አቀፋዊ የደኅንነት እና የልማት ችግሮችን ለመፍታት ያላትን ሚና አስመልክቶ እንዳሉት “በአሁኑ ጊዜ የአፍሪካ ሀገራት በዚህ ምክር ቤት ጭምር በድርድር ጠረጴዛ ላይ መቀመጫ መከልከላቸውን ቀጥለዋል” ሲሉ አፍሪካ ትኩረት እንዳጣች ገልጸዋል። በመኾኑም አፍሪካ በዓለም ሰላም እና ደኅንነት ድምጿን ማሰማት እንደሚገባት ገልጸው ይኽንን እውን ማድረግ የሚቻለው የአፍሪካ ሀገራት በእኩልነት በዓለም አቀፍ የአስተዳደር መዋቅር ውስጥ መሳተፍ ሲችሉ እንደኾነ አስረድተዋል።
በፀጥታው ምክር ቤት አናሳ የኾነውን የአፍሪካን ቋሚ ውክልና ማስተካከል እንዲሁም የእዳ አያያዝን ማሻሻልን ጨምሮ የዓለም የገንዘብ ሥርዓት መስተካከል እንዳለበት ጠቁመዋል። በአፍሪካ ያሉ ግጭቶች አብቅተው አሕጉሪቷ ሰላም ማግኘት አለባት ብለዋል፡፡ ተመድ የአፍሪካን ሰላም ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት ሙሉ በሙሉ እንደሚደግፈው አንስተው ይኽም በአፍሪካ ኅብረት ዋና የትኩረት ማዕከል በኾነው የጠብመንጃ እንቅስቃሴን በማስወገድ እንደኾነ አንስተዋል።
እንደ ዢንዋ ዘገባ የአፍሪካ ኅብረት እና ተመድ ግጭቶች ከመባባሳቸው በፊት ለማርገብ፣ ከተከሰቱም በብቃት ለመቆጣጠር እና መፍትሄ ሲያገኙም ደግሞ ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር በጋራ መስራታቸውን እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!